ቀጥታ፡

ኢቢሲ ከአገር ባለፈ በአፍሪካ አውድ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ሚዲያ ለመሆን መስራት ይጠበቅበታል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

 አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015  (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ከአገር ባለፈ በአፍሪካ አውድ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ሚዲያ ለመሆን መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አዲሱን የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የኢቢሲ አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በተቋም ግንባታ ረገድ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያዊን መልዕክትን በድንጋይ ከመቅረጽ ጀምሮ ቀደምት የመረጃ ልውውጥ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች ስለመሆናቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት እድገት ካስመዘገቡ ዘርፎች መካከል ሚዲያ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢቢሲ ይህንን በሚመጥን መልኩ መደራጀቱን ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢቢሲ ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት የሚያገለግልና በአፍሪካ አውድ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ሚዲያ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

ሚዲያ ለአንድ አገር ትርክት ግንባታ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም ኢቢሲ ድምጽ የሚያሰማ ብቻ ሳይሆን ድምጽ የሚፈጥር ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ብሎም የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ልእልና ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ላይ እንዲሁ ጎልቶ መውጣት አለበት። 

ዛሬ የተመረቀው የኢቢሲ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በኢትዮጵያ የሚገነቡ ተቋማት ረዥም ዓመታትን እንዲያገለግሉ ተደርገው እየተሰሩ ስለመሆናቸው የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ለስራ ምቹ፣ ሳቢና ፈጠራን በሚያበረታታ መልኩ ተቋምን በመገንባት ረገድ ምሳሌ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም