ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አዲሱን የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ መርቀው ከፈቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አዲሱን የኢቢሲ ሚዲያ ኮምፕሌክስ መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ ሰኔ 28/2015 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ አዲስ የተገነባውን ዘመናዊ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሚዲያ ኮምፕሌክስ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢቢሲ ድምፅ የሚያስተጋባ ሳይሆን ድምፅ የሚፈጥር ሚዲያ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።
ለመንግስት ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት የህዝብ ድምፅና ልሳን መሆን አለበት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያ ዓለምን ከሚለውጡ አበይት መሳሪያዎች አንዱ እንደመሆኑ ሀገራችንም በዘርፉ እንድትቀየር ኢቢሲ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
አዲሱ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ዓለም በደረሰበት የሚዲያ ቴክኖሎጂ የተደራጁ ስቱዲዮዎች ያሉት ሲሆን ኢቢሲ "ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ቃል በሁሉም አማራጮቹ አዳዲስ ይዘቶችን እና አቀራረቦችን አካቶ ወደ አድማጭ ተመልካች ለመድረስ ዝግጅቱን መጠናቀቁም ተመላክቷል።