የፌዴሬሽን ምክር ቤት "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" 12ኛው የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" 12ኛው የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ወሰነ
አዲስ አበባ ሰኔ 28/ 2015 (ኢዜአ) የፌደሬሽን ምክር ቤት "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" 12ኛው አዲሱ የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ወሰነ።
ምክር ቤቱ ባካሄደው 2ኛ መደበኛ ጉባኤው ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ስር በነበሩ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባካሄዱት ህዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል ለመደራጀት ድምፅ መስጠታቸውን ተከትሎ አዲስ ክልል እንዲደራጅ ወስኗል።
"የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዲዮ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በአሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ አስተዳደር ወሰንና ሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ፍቅሬ አማን አዲስ ክልል እንዲደራጅ የሚያደርገውን የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ክልል ለመመስረት ላቀረቡት ጥያቄ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ መምራቱን አውስተዋል።
በዚህም መሰረት ቦርዱ ያቀረበውን የህዝበ ውሳኔ ሂደት፣ አፈጻጸምና ውጤት በመመርመር ስድስቱ ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች በጋራ "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" ሆነው ለመደራጀት ድምጽ መስጠታቸው በመረጋገጡ የውሳኔ ሀሳቡ መቅረቡን ጠቅሰዋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን ህገ-መንግስታዊ መብትን የሚመልስ በመሆኑ እንደሚደግፉት አስተያየት ሰጥተዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ "የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል" 12ኛው የኢትዮጵያ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አዲሱ ክልል በይፋ መመስረቱን በመግለጽ የስልጣን ርክክብ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ቀሪዎቹ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት እንደሚቀጥሉም ነው አፈጉባኤው የገለጹት።