የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከየትኛውም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊቃጡ ከሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን መከላከል የሚያስችል አቅም እየገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከየትኛውም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊቃጡ ከሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን መከላከል የሚያስችል አቅም እየገነባ ነው
አሶሳ ሰኔ 27 / 2015 ዓ.ም (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከየትኛውም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊቃጡ ከሚችሉ የፀጥታ ችግሮች መከላከል የሚያስችል አቅም እየገነባ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ለምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በአሶሳ ከተማ የተገነባ ካምፕ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ኢትዮጵያ ከፈተና አልፋ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል የፀጥታዋም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀልን በመከላከል ግዙፍ አቅም እየፈጠረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ይህም በአገሪቱ ላይ ከየትኛውም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊታሰቡ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን መመከት ያስችላል ብለዋል፡፡
ፌደራል ፖሊስ ለሠላም የሚከፍለውን መስዋእትነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ጀኔራል አስታውቀዋል፡፡
በአሶሳ የተገነባው የፈጥኖ ደራሽ ካምፕ በሌሎች አካባቢዎችም በማስፋፋት የሠራዊቱን አቅም በበለጠ ለማጠናከር የሚደረግ ጥረት መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የአሶሳው ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ለክልሉ ፖሊስ ጭምር የሚያገለግል እንደሆነ ጠቁመው፤ ሠራዊቱ የአካባቢውን ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የልማት ስራዎችን በማከናወን የህዝብ አጋርነቱን ያስቀጥላል ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው ከሃገራዊ ለውጡ በኋላ ዘመን ተሻጋሪ ተቋም ለመገንባት በተደረገው ጥረት ውስጥ የፌደራል ፖሊስ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ ወደ ሠላም እንዲመለስ የፌደራል ፖሊስ ያደረገውን ከፍተኛ ጥረት የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም የተከናወነው ሠራዊቱ ከክልሉ ህዝብ ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የኢንቨስትመንትን ጨምሮ በሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎች የፌደራል ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል የሚደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት አቶ አሻድሊ ገልጸዋል፡፡
የምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ካምፕ ከ153 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የተደረገ ሲሆን፤ የአስተዳደር፣ የመኖሪያ፣ መመገቢያ ህንጻችን እና የስፖርት ማዘወተሪያ እንዳካተተም በዚሁ ጊዜ ተመልክቷል፡፡
በምረቃው ሥነስሥርዓት ላይ የታደሙ የፌዴራልና የክልሉ አመራሮች ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን ማኖራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡