ቀጥታ፡

በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት የለውጥ ሂደትና ከፍታ ያሳየ ነው-  የሚዲያ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ) በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት የለውጥ ሂደትና ከፍታ ያሳየ መሆኑን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የሥራ ኃላፊዎች ተናገሩ። 

ከመንግሥትና ከግል መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ አመራሮችና ጋዜጠኞች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የጤና አውደ-ርዕይ ጎብኝተዋል።

ከጎብኝዎቹ የሚዲያ ኃላፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ተፈራ በቀለ፤ በአውደ-ርዕዩ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት ደረጃ ከፍታ ማየት የቻልንበት ነው ብለዋል።


 

ለእይታ የቀረቡት ምርትና አገልግሎቶችም የዜጎችን ጤና በማስጠበቅ ረገድ የላቀ ፋይዳ ያላቸው መሆኑንና የቴክኖሎጂና የአሠራር ለውጡን ተገንዝበናል ነው ያሉት።

የመገናኛ ብዙኃን በጤናው ዘርፍ ለሚሰሯቸው ተግባራት በእውቀት ላይ የተመሰረተ በማድረግ ሕብረተሰቡን ለማስገንዘብ ጉብኝቱ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎቹ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የጤና አውደ-ርዕይ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት የለውጥ ሂደትና ከፍታ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ግዛቸው ጋቢሳ፤ በጉብኝቱ ኢትዮጵያ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤናው ዘርፍ ለማሳካት የወጠነቻቸውን ግቦች እውን ለማድረግ ውጤታማ ሥራ እየሰራች መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙኃኑ ጉብኝትም በጤናው ዘርፍ ያሉ ውጤታማ ሥራዎችን በእውቀት ላይ ተመስርተው ለመዘገብ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።


 

የናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤን.ቢ.ሲ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ፤ የአውደ-ርዕዩ ጉብኝት ጤናማና አምራች ዜጋ እንዲፈጠር በሚደረገው ጥረት በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃን ለማኅበረሰቡ ለማድረስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ለማሳወቅም መሰል አውደ-ርዕዮች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በጤና አውደ-ርዕዩ ላይ የቀረቡ ምርትና አገልግሎቶችን ሕብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ለማስቻል መገናኛ ብዙኃን በስፋት ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።

"የመጪው ትውልድ ጤና" በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር ለዕይታ የተዘጋጀው አውደ-ርዕይ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በዘርፉ የምርምር ሥራዎችን ያከናወኑ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለዕይታ አቅርበዋል፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሰላምና ደኅንነት ከፍተኛ መኮንኖች፣ መምህራንና ተማሪዎች፣ የጤና ሙያተኞች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል። 

ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎንም የጤናውን ዘርፍ ማሻሻል የሚያስችል የጥናት፣ የምርምር፣ የስትራቴጂና ፖሊሲ አቅጣጫ የሚደግፉ ልዩ ልዩ መድረኮችም ተካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም