በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓትን ከዓለም ተሞክሮ ጋር ያስተሳሰረ የሰላም ግንባታ ሥልጠና ሰነድ ተዘጋጅቷል - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓትን ከዓለም ተሞክሮ ጋር ያስተሳሰረ የሰላም ግንባታ ሥልጠና ሰነድ ተዘጋጅቷል - ኢጋድ
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 27 / 2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ሥርዓትን ከዓለም ተሞክሮ ጋር ያስተሳሰረ የሰላም ግንባታ ሥልጠና ሰነድ መዘጋጀቱን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት /ኢጋድ / ገለጸ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከኢጋድ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ወጥነት ላለው የሰላም ግንባታ ሥራ የሚውል "የሰላም ግንባታ ማሰልጠኛ ሰነድ" አዘጋጅቷል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት /ኢጋድ/ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ለአባል ሀገራቱ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር እየሰራ ይገኛል፡፡
የኢጋድ ሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ሲራጅ ፈጌሳ፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢጋድ የቀጣናውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከአባል ሀገራቱ ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያም ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መንግሥት የጀመረውን ሰላም የማስፈን ሂደት የሚያግዝ "የሰላም ግንባታ ማሰልጠኛ ሰነድ" አዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
ሰነዱ የኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ የሚመራበት ማኑዋል መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ እሴት ዓለም ከደረሰበት ሳይንሳዊ ደረጃ ጋር በማስተሳሰር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ረገድ ሰነዱ የጎላ አበርክቶ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ሰላም በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ ቀጣይነት ያለው የትውልድ ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በትውልድ ቀረፃ ሂደት የኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ብቻቸውን ውጤታማ ስለማይሆኑ ከሳይንሳዊ ስልቶች ጋር ማጣመር እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የሰነዱ ዝግጅት መሪ ፕሮፌሰር ጀይላን ወልዬ፤ ግጭቶችን ለመፍታትና ሰላምን ለመገንባት አንድ ዓይነት የሆነ ዘዴ የለም ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሰላምን ለመገንባት አካታችና አሳታፊ የሰላም ውይይት መኖር አማራጭ የሌለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሰላም በዘላቂነት ሰፈነ የሚባለው ለግጭት የማይበገር ትውልድ መፍጠር ሲቻል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጀይላን፤ ሰላም ለማስፈን ሰላማዊ ውይይት ብቸኛ አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
ሰላም የሁሉንም የልማትም ሆነ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚመለከት የጋራ ሥራ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ጀይላን፤ ለሰላም ግንባታ ሁሉም አካላት አስተዋጽዖ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፤ የሰላም ግንባታ ሥልጠና ሰነድ ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ የተሻለ መፍትሔ የሚጠቁም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰነዱን የኢትዮጵያን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ከሳይንሳዊው ጋር ያጣመረ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ሰላምን የሥራቸው አንድ አካል እንዲያደርጉት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የሰላምና የልማት ጉዳይ የማይነጣጠሉ በመሆናቸው ሁሉም ተቋማት የሰላም ግንባታ ማሰልጠኛ ሰነዱን ሊጠቀሙበት ይገባል ነው ያሉት።