የስደተኞችና ስደተኞች አስተናጋጅ አካባቢዎች የዲጂታል ግንኙነትና አካቶ ፕሮጀክቶች ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስደተኞችና ስደተኞች አስተናጋጅ አካባቢዎች የዲጂታል ግንኙነትና አካቶ ፕሮጀክቶች ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦ የስደተኞችና ስደተኞች አስተናጋጅ አካባቢዎች የዲጂታል ግንኙነትና አካቶ ፕሮጀክቶች ሊተገበር መሆኑ ተገለፀ፡፡
የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ከአለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት እና ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞችና ስደተኛ አስተናጋጅ ማህበረሰቦች የዲጂታል ግንኙነትና አካታችነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለስደተኞች ማዕከላትና ለአስተናጋጅ ማህበረሰቦች የሚሰጠውን አገልግሎት ከማሻሻል በተጨማሪ ስደተኞችን ለማስተማር እና እንደ ቤተ-መጻሕፍት ያሉ የትምህርት ግብአቶችን፣ የባንክ እና የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እና አዳዲስ ክህሎቶችን የመማር እና የሥራ እድላቸውን ለማሻሻል ያስችላል ተብሏል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ የስደተኞች ጉዳይ ከተለመደው የመጠለያ፣ የምግብና አልባሳት ጉዳይ ባለፈ የ digital ግንኙነትና ተደራሽነትን አጀንዳ በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
በዚህም የስደተኞችን ሁኔታ ለማሻሻልና አቅማቸውን ለማጎልበት እንዲሁም እድላቸውን ለማስፋት እጅግ መሠረታዊና አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለእዚህም የአለም አቀፍ የቴሌኮም ህብረት (UN-ITU) አዲሷን ተመራጭ ሀላፊ ዶሬን ቦግዳን እንዲሁም የ UNHCR ምክትል ኮሚሽነር ኬሊ ክሌመንትስን አመስግነዋል።
አያይዘውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ይህንኑ እውን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ገልጸው የአለም አቀፍ ቴሌኮም ህብረት ትብብርና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ስደተኞችና ስደተኛ አስተናጋጅ አካባቢዎችን በዲጂታል ተደራሽነትና አካታችነት ማዕቀፍ ከመደገፉ ጥረት ጎን ለጎንም የትምህርት ቤቶችን ሁኔታ ማሻሻልና አቅማቸውን ከማሳደግ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን አዲስ ሀገራዊ ንቅናቄ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የትምሀርት ቤቶችን አቅም ለመገንባት የተጀመረውን ኢኒሼቲቭ በቀጣይ የአለም አቀፉ ቴሌኮም ህብረት እንዲደግፍ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
አያይዘውም የ"Connect to Recover" ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን የፕሮጀክት ፕሮፖዛል ተቀርጾ ለህብረቱ መላኩን በማስታወስ ሀላፊዋ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉትና ኢትዮጵያም ተጠቃሚ እንድትሆን እንዲደግፉ ዶክተር በለጠ ጥሪ አቅርበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በቅርብ አመታት አስቸጋሪ የውስጥ ሁኔታ ገጥሟት የቆየች መሆኑን አውስተው ይህም ሆኖ ስደተኞችን ለመቀበል እጇን ያላጠፈች ለጋስ ሀገር መሆኗ ልዩ ትኩረትና አድናቆት ሊሰጣት የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም ይህ በአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ITU እና በ UNHCR የተጀመረው ስደተኞችንና አስተናጋጅ ማህበረሰቦችን በዲጂታል ግንኙነትና አካታችንት ማዕቀፍ ውስጥ የማስገባት ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እንዲሆን ቀጣይነት ያለው የግንኙነት ስርአት ሊዘረጋለት ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቋማቱ ትስስር ፈጥረው እንዲሰሩ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ዳይሬክተር ጀኔራል ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከሚያስተናግዱ ሀገራት አንዷ መሆኗን አስታውሰዋል።
ስደተኞች የመማርና የመስራት አቅም ያላቸው ቢሆኑም እንደሌላው ዜጋ በቂ የሆነ የኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶች ባለማግኘታቸው ችግር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም በኢንተርኔት ላይ ያለው አቅርቦት አናሳነት በኦንላይን መማርም ሆነ የፋይናንስ ግብይት ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት በተቋሞቹ በኩል የስደተኞቹን ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው በተለይ የኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ረገድ ያደረጋቸውን ጥረቶች እንደምሳሌ አድንቀዋል።
በውይይቱ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች፣ የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና አምባሳደሮች ሀሳቦችን አንስተው ውይይት መደረጉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በማጠቃለያውም የአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ዋና ዳይሬክተር ዳሮን ቦግዳን የስደተኞችና ስደተኛ ተቀባይ አካባቢዎችን በዲጂታል ግንኙነትና አካታችንት ለመደገፍ የትምህርት እና ጤና ሁኔታን ለማሻሻል የተቀረጸውን አዲስ የመሸጋገሪያ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
አጋር አካላትም ይህንኑ እንዲደግፉና የስደተኞችን ህይወት ለማሻሻል ጥረቱን እንዲያግዙ ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ ማቅረባቸውም ተጠቅሷል።