በጥናት የተደገፈ የምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት ይሰራል- ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
በጥናት የተደገፈ የምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት ይሰራል- ዶክተር ፍጹም አሰፋ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015 (ኢዜአ) በጥናት የተደገፈ የምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ፤ በኢትዮጵያ "ሁሉን አቀፍ የምርታማነት አቅም ማሳደጊያ ፕሮግራም" ጥናት በተመለከተ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል።
በመድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ላለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ያሉበትን ክፍተቶች ለመለየት የሚያስችል ጥናት ማድረጉን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ለምርታማነት መጨመር፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የሰው ኃብት ልማትና ሌሎች የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ ያሉ ክፍተቶች በጥናቱ መለየታቸውንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በጥናት የተደገፈ የምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን የአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እንዲሳካ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉን አቀፍ የምርታማነት አቅም ማሳደጊያ ፕሮግራም ከሌሎች ፕሮግራሞች ጋር ተሰናስሎ ይተገበራል ብለዋል።
የአሥር ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ለማስፈጸምና የፖሊሲ ማሻሻያ ምክረ-ሃሳብ ግብዓት በመሆን ቁልፍ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የኢትዮጵያን የማምረት አቅም ለመጨመር በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው መልካም ዕድል የፈጠረ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የግብርናና መሠረተ- ልማት፣ የአቅም ግንባታ፣ የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የአገልግሎት ክላስተሮችን በመለየት ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ተናግረዋል።
የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ከ50 በመቶ ወደ 85 በመቶ የማድረስ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን 5 ሚሊየን የማድረስ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማሳደግ ዕቅድ መያዙንም አንስተዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና የአሥር ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ ለማሳካት ሁሉን አቀፍ የምርታማነት አቅም መጨመር ፕሮግራም ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስተር ፓውል አኪዩሚ፤ በየትኛውም አገር የኢኮኖሚ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች የሚያጋጥሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ችግሮች ስለመኖሩ አንስተዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ምርታማነትን የማሳደግ ሁሉን አቀፍ የልማት ፕሮግራም የችግሩ መፍትሔ ከመሆን ባለፈ በአሥር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።