የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር አለባቸው-የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር አለባቸው-የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም ትብብራቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች ገለጹ።
የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች መካከል አንደኛው ሲሆን፤ ለአብነትም የዓለም ሙቀት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በአማካኝ በ1 ነጥብ 2 ዲግሪ ሴልሺዬስ ጨምሯል፡፡
በዚህ ምክንያትም ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የዝናብ ወቅት፣ ስርጭትና መጠን መዛባት እንዲሁም የአካባቢ መራቆት የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በዓለም የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ከሚደርስባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ማዕከልና በኖርዌይ የአየር ንብረት ማዕከል ከፍተኛ የአየር ንብረት ተመራማሪ ዶክተር ተፈሪ ደጀኔ፤ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም ያላቸው አቅም ውስን መሆን ችግሩን የከፋ አድርጎታል ይላሉ፡፡
ቀጣናው በዝናብ ስርጭትና መጠን መዛባት፣ ተከታታይ ድርቅ እንዲሁም በጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ እየተጠቃ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡
ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተጽእኖውን ለመቋቋም ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ በመርሃ ግብሩ ለአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ትኩረት መሰጠቱ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን መቋቋም የሚችል ግብርና ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ተቋም (AICCRA) የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር ዳዊት ሰለሞን በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን በተለየ ሁኔታ እየጎዳ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ተጽእኖው ከፍተኛ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት(ኢጋድ) የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን በማስተባበር ጭምር ተጽዕኖውን ለመቋቋም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም የቀጣናው አገራት ትብብር ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ነው ምሁራኑ የተናገሩት፡፡
እንደ ዶክተር ተፈሪ ደጀኔ ገለጻ፤ የአየር ንበረት ለውጥን መቋቋም ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ስራ አይደለም፡፡
ከዚህ አኳያ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከተቋም ለተቋም ባሻገር በአገር ደረጃ በጉዳዩ ላይ በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር ዳዊት ሰለሞን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ትብብር ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለባት ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡