የማዕድን ምርት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ህገ ወጥ ድርጊትን ለማስቆም በመንግስት የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ማዕድን ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የማዕድን ምርት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ህገ ወጥ ድርጊትን ለማስቆም በመንግስት የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ማዕድን ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦የማዕድን ምርት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ድርጊት ለማስቆም በመንግስት የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዮስ፤ የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭነቱ ተረስቶ የቆየ መሆኑን ይናገራሉ።
በለውጡ ዓመታት ግን የማዕድን ዘርፉን በብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስርዓቱ ዋነኛ የዕድገት ምንጭ በማድረግ ወደ ስራ ተገብቶ አሁን ላይ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚና ለኢንዱስትሪው ዋነኛ የግብዓት ምንጭ እንዲሆን የማድረግ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የማዕድን ዘርፍ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው በቀጥታና እሴት ተጨምሮ ከሚላኩ ማእድናት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዓለም የኢንዱስትሪ አቢዮትን በማካሄድ በርካታ አገሮች እድገት ማምጣታቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያም በአዲስ ምዕራፍ በዚሁ አግባብ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት የማእድን ዘርፉ የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጀርባ ያሉ ኃይሎች በዘርፉ ላይ ህገወጥ ምርትና ዝውውር በመፈጸም ችግር ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
የማዕድን ዘርፉን በህገ-ወጥ መንገድ የሚያመርቱና ከሀገር የሚያሸሹ ዜጎችና የውጭ አገር ሰዎች መኖራቸው ተደርሶበታል ብለዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመገምገም ሁሉም የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት ብሔራዊ ካውንስል በማቋቋም ማዕድናት በስፋት በሚመረቱባቸው አካባቢዎች የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የማዕድናት ምርት ወደ ማዕከላዊ ባንኮች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲገቡና ተኪ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ለኢንዱስትሪዎች እንዲደርሱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር በተለይ የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት በህገወጥ መንገድ በማምረትና ከሀገር በማሸሽ ላይ ወንጀል በተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
የመንግስት እርምጃ የማዕድን ዘርፉ ላይ ህግን አክብረው ለሚሰሩት ዋስትና የሚሰጥና የህገ ወጦችን እንቅስቃሴ የሚያስቆም መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
በህጉ መሰረት የሚሰሩ የሀገር ውስጥ ባህላዊ የወርቅ አምራቾችና ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎች በስራቸው ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራው ተጠናከር መቀጠሉን በማንሳት፤ ህገወጥ የማዕድን እንቅስቃሴን የማክሸፍ ስራም በመሰራቱ ወርቅ አምራች በሆኑት አካባቢዎች የሚመረተው መጠን እየጨመረ ነው ብለዋል።
በመንግስት እየተከናወነ ያለው ጥብቅ እርምጃ በህጋዊ መልኩ ለሚሰሩ የሀገር ውስጥና የውጭ አምራቾች መልካም እድል የፈጠረ ነው ብለዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕገወጥ የወርቅ ምርትና ግብይት ተግባር ተሰማርተው የተገኙ 29 የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልገሎት መግለፁ ይታወቃል።