በጤና መድህን አገልግሎት 56 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - የጤና መድህን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በጤና መድህን አገልግሎት 56 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - የጤና መድህን አገልግሎት
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦በአገር አቀፍ ደረጃ በጤና መድህን አገልግሎት 56 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከአስር ዓመት በፊት በ13 ወረዳዎች የተጀመረው የጤና መድህን አገልግሎት አሁን ላይ እየተስፋፋ መጥቶ በሺዎች በሚቆጠሩ ወረዳዎች ተዳርሷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት አበበ፤ በዓለም አቀፍ ተሞክሮ መነሻነት በኢትዮጵያ ሁለት አይነት የማህበረሰብ አቀፍ እና የማህበራዊ ጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መደበኛ ባልሆነ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ አርሶና አርብቶ አደሮችን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎትም የመንግስት ሰራተኞች፣ ጡረተኞችን ጨምሮ ሌሎች በመደበኛ ወርሃዊ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ለጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በተለይም ለአርብቶ አደሩ ምቹ የሆነ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉም ተናግረዋል።
ከአስር ዓመት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ አሁን ላይ በ1 ሺህ 3 ወረዳዎች እየተተገበረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በጤና መድህን አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ 56 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
የአባልነት ክፍያ ለመፈጸም የተቸገሩ 10 ሚሊዮን ዜጎችንም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የጤና መድህን አገልግሎት በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ ከደንበኞች እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብም በየዓመቱ እድገት እያሳየ መቷል ብለዋል።
በ2013 እና 2014 ዓ.ም በቅደም ተከተል 4 እና 5 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታውሰው በ2015 ዓ.ም ደግሞ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ከተሞች ላይ የአባልነት መዋጮ ክፍያ ቀጥታ በባንክ የሚሰበሰብ ሲሆን የባንክ አገልግሎት በሌለባቸው አካባቢዎችም በደረሰኝ ተዘጋጅቶ ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል።