ቀጥታ፡

በመጪው ሐምሌ ወር የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ ይቀጥላል--የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦ በመጪው ሐምሌ ወር በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ሆሮጉድሩ፣ ቄለም ወለጋ፣ አርሲና ባሌ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ አመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ ዞን፣ ሰሜን ሸዋ ዞኖች፤ እንዲሁም በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ፣ ደቡብ እንዲሁም ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኛው ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።

ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ በአፋር ክልል የሚገኙ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ፣ ድሬድዋ፣ የሶማሌ ክልል ሰሜናዊ ዞኖች፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ በብዙ ቦታዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖራቸው ተመላክቷል።

የክረምቱ ዝናብ የመኸር እርሻ ለተጀመረባቸው አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ነው የተጠቆመው፡፡

ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች የአፈር መሸርሸር እንዳይከስት እንዲሁም ውሃ በማሳ ላይ በመተኛት ጉዳት እንዳያደርስ የጎርፍ መከላከያ እርከኖችና ማፋሰሻዎችን መስራት እንደሚገባም ነው ኢንስቲትዩቱ ያስታወቀው፡፡

በዝናብ አጠር አካባቢዎችም ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም