ቀጥታ፡

ዜጎች የሀገራዊ ምክክር ጥቅሞችንና ዓላማዎችን በውል  በመረዳት ያልተቆጠበ ተሳትፎ  ማድረግ አለባቸው -- የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን 

ቦንጋ ሰኔ 27 /2015 (ኢዜአ) ዜጎች የሀገራዊ ምክክር ጥቅሞችንና ዓላማዎችን በውል በመረዳት ያልተቆጠበ ድጋፍና ተሳትፎ  እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር  ሙሉጌታ አጎ ጠየቁ።

ሀገራዊ ምክክር አንድ ወጥ ሀሳብና አንድ ወገን ብቻውን የሚመክርበት ሳይሆን፣ በየአጀንዳው የተለያዩ ሀሳቦች፣ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መብቶች የሚወከሉበትና ምክክር እንደሚደረግበትም ገልጸዋል።

ምክክሩ የተለያዩ ሀሳቦችን የሚወክሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወከሉበት ብዝኃነት ያለው መድረክ በመሆኑም ለስኬታማነቱ ሁሉም ዜጋ ያልተቆጠበ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርግ ኮሚሽነር ሙሉጌታ ጠይቀዋል። 

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን የገለጹት ኮሚሽነር ሙሉጌታ፣ በአሁኑ ሂደት በክልል ደረጃ አጀንዳ የሚያዋጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመለየት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

በዚህ ረገድ በክልል ደረጃ የህብረተሰብ ወኪሎችን የመምረጥ ስራ በተወሰኑ ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር መጀመሩን ገልጸዋል።

ከነዚህም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋና ቤንች ሸኮ ዞኖች ከተለያዩ መሰረታዊ ማህበራት የተወጣጡና በክልል ደረጃ በምክክሩ የሚሳተፉትን ለመምረጥ በተሰናዳው መድረክ ላይ ከ8 ሺህ 500 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ተወካዮችን የመምረጥ ሂደት ፍፁም ሰላማዊ፣ አሳታፊና አካታች እንደነበረ ያወሱት ኮሚሽነር  ሙሉጌታ፣  ህብረተሰቡ 'እኔም በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል' በሚል ጠንካራ እሳቤ ለስራው መሳካት እያደረገ ያለው ተሳትፎ አመርቂ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ከወረዳ እስከ ክልል የሚሰበሰቡ አጀንዳዎችን አንድ ላይ ጨምቆ ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡትን  እንደሚዘጋጁ ገልጸው፣ ይህም የክልል ወኪሎችን የመምረጥ ስራ በሁሉም ክልሎች ሲጠናቀቅ ይከናወናል ብለዋል።  
 

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማካሪ ኮሚቴ አባል አቶ አሰፋ ገብረማሪያም ኮሚቴው ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሂደት አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ጉዳዮችን በጥናት አስደግፎ ለማቅረብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ችግሮች በምክክርና በውይይት ተፈተው በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት የመኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ውይይት መድረኮች ከሚያነሳቸው ሀሳቦች መገንዘብ እንደሚቻልም ነው አቶ አሰፋ የገለጹት።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ችግሮችንን በምክክር በመፍታት የጋራ ሀገርን በጋራ የመገንባት ሂደት ውስጥ ድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል።

ችግሮችን በምክክር መፍታት የሰለጠነ አካሄድ መሆኑን ያነሱት  አቶ አሰፋ፣ እንደ ሀገር በማያግባቡን  መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ውሳኔ ላይ መድረስ አስፈላጊ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተውታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም