የፌደራል ፖሊስ ሠላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራል ፖሊስ ሠላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አሶሳ ሰኔ 27 /2015(ኢዜአ) ፡- የፌደራል ፖሊስ ሠላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡
በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የምዕራብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ በአሶሳ ከተማ ያስገነባውን ካምፕ ዛሬ አስመርቋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ፌደራል ፖሊስ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ግዙፍ አቅም እየፈጠረ ነው።
የፌደራል ፖሊስ ሠላምን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው፤ በአሶሳ ከተማ ከተመረቀው በተጨማሪ በየክልሉ የሠራዊቱን አቅም የሚያጠናክሩ ካምፖች እየተገነቡ ነው ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው፤ ክልሉ ወደ ተረጋጋ ሠላም እንዲመለስ የፌደራል ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሏል ብለዋል።
በክልሉ በአሁኑ ወቅት በማዕድናትና በሌሎችም ዘርፎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ኢንቨስትመንቱ እንዲጠናከር የፌደራል ፖሊስ እገዛ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዝግጅቱ ታዳሚዎች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።