ቀጥታ፡

በ"ገበታ ለትውልድ" የሚገነባው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ለአካባቢው ቱሪዝም እድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦በ"ገበታ ለትውልድ" የሚገነባው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ለአካባቢው ቱሪዝም እድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውን የአርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ትናንት አስቀምጠዋል፡፡

የሪዞርቱ ግንባታም በርካታ የተፈጥሮ መስህብ ላለው የአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው ቱሪዝም መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡


 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤  የሪዞርቱ ግንባታ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የሪዞርቱ ግንባታ የውጭ አገር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሳተፉ መነሳሳት እንደሚፈጥርም እንዲሁ፡፡

ሪዞርቱ ከአካባቢው ባለፈ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን በየአካባቢያችን ያሉ ጸጋዎችን በማልማት አገራችንን በአጭር ጊዜ መለወጥ እንችላለን" ሲሉም አፈ-ጉባኤው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአስደናቂ ባህል፡ ታሪክና ተፈጥሮ ባለቤት መሆኗን ተናግረዋል፡፡


 

የቱሪዝም ሃብቶችን በትብብር በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሻሻል እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት ግንባታ ዘርፉን ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡

የኮንፍረንስ ሪዞርት ግንባታው ከገቢ ምንጭነት ባሻገር የአገር ገጽታን በበጎ ጎኑ የሚለውጥ መሆኑንም  ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በዋናነት ኢትዮጵያ ያሏትን አምቅ የመልማት አቅሞች ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት የሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ናቸው፡፡


 

እነዚህ ፕሮጀክቶች  በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት የሚገነቡ መሆናቸው ደግሞ ዘመን ተሻጋሪ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በኢትዮጵያ ያሉ ሌሎች የልማት አቅሞችን በማውጣት አገር ለመለወጥ በትብብር መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በ"ገበታ ለትውልድ" ፕሮጀክት አማካኝነት  የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የቱሪዝም አቅሞችን ለልማት ለማዋል እንደሚሰራ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም