ኢጋድ የአባል አገራትን የጸጥታና ደህንነት ተቋማት አቅም በመገንባት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ የአባል አገራትን የጸጥታና ደህንነት ተቋማት አቅም በመገንባት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር የአባል ሀገራትን የጸጥታና ደህንነት ተቋማት አቅም በመገንባት ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል የተቋሙ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ሲራጅ ፈጌሳ አስታወቁ።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና እድገት ማረጋገጥ ያስችላል የተባለና የሰላም ሚኒስቴር እና ኢጋድ በጋራ ባዘጋጁት የሰላም ሰነድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።
የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ሲራጅ ፈጌሳ እንዳሉት የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ድንበር ተሻጋሪ የግጭት መንስኤዎች በመለየት፣ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እና ለቀጣናው ሰላም የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው።
ሽብርተኝነትን መከላከል፣ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ ሰላምን መፍጠር እንዲሁም ከግጭት በኋላ መልሶ መገንባት ላይ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም የሰላም ሂደቱን ማጽናትና ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችል የሰላም ግንባታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡን አንስተዋል።
ሰነዱ የማህበረሰቡን ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ከሳይንሳዊ አሰራር ጋር በማጣመር የኢትዮጵያን ሰላም ሂደት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል መሆኑን አቶ ሲራጅ የገለጹት።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በበኩላቸው የሚኒስቴሩ ዋና ተልዕኮ አዎንታዊ ሰላም መገንባት መሆኑን ገልጸው ስልጠና፣ ውይይት፣ ምክክር ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት ብቸኛ አማራጮች ናቸው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የሚያዘጋጃቸው መድረኮች በውይይት የዜጎችን ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል አውድ መፍጠር ማስቻልን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ኢጋድ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሰላም ሰነድ የኢትዮጵያ ማህበራዊ እሴት ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያዛመደ በመሆኑ ለሰላም ግንባታው የጎላ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።