ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፓሪስ ዓለም አቀፍ የፋሽን ንግድ አውደ ርዕይ ላይ የአገር ውስጥ ምርቶቿን እያስተዋወቀች ነው

አዲስ አበባ ሰኔ 27/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በፓሪስ ዓለም አቀፍ የፋሽን ንግድ አውደ ርዕይ ላይ የአገር ውስጥ ምርቶቿን በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

‘TexworldevolutionParis’ በሚል ስያሜ የሚካሄደው አውደ ርዕይ ትናንት ተጀምሯል።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ ተገኝተዋል።

አውደ ርዕዩ በፋሽን ኢንዱስትሪው የሚገኙ አቅራቢዎችን የሚያገናኝ እና ዓለም አቀፍ ገዢዎች የተለያዩ የፋሽን ምርቶችን የሚገዙበት አማራጭ የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ በሽመና እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተመረቱ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ የቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች እና ፈጠራ የታከለባቸው የፋሽን ስራዎች የቀረቡ ሲሆን ከ130 አገራት የተወጣጡ 29 ሺህ ዓለም አቀፍ ገዢዎች ተሳትፈውበታል።

በዚህ አውደ ርዕይ ላይ የኢትዮጵያ አምራቾች በአገር ውስጥ የተመረጡ የባህል አልባሳት እና የተለያዩ ምርቶች (Made In Ethiopia) በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅ እና አዳዲስ ገዢዎች ለመሳብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።

በፓሪስ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ የፋሽን ንግድና አውደ ርዕይ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን አውደ ርዕዩ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም