ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ስርዓት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች አምራች ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ስርዓት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች አምራች ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው - የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ)፦ ዘመናዊ የጤና አገልግሎት ስርዓት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች አምራች ማህበረሰብ በመገንባት ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች ገለጹ፡፡
የሚኒስቴሩ አመራሮች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የጤና አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ አውደ ርዕዩ የሕብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንና ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለችበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የሕብረተሰብ ጤና ከምርት እና ምርታማነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ገልጸው በዚህ ረገድ በጤናው ዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
የጤና አገልግሎቱን ለአካል ጉዳተኞች እና ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መስፋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ ታዳጊዎች በጤናው ዘርፍ ለመሰማራት ራዕይ ሰንቀው እንዲሰሩ መነሳሳት ይፈጥራል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመጀመሪያውን የጤና አውደ-ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ሰኔ 13 2015 በይፋ መክፈታቸው ይታወቃል።
የተለያዩ ተቋማት አውደ ርዕዩን እየጎበኙ ሲሆን እስከ ሐምሌ 12 2015 ይቆያል።