ቀጥታ፡

አየር መንገዱና ጉምሩክ ኮሚሽን ፈጣን አገልግሎት በጋራ ለመስጠት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ)፦በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና በሌሎችም የአገራችን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ለመንገደኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ የጉምሩክ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ናቸው፡፡

አቶ መስፍን ጣሰው ከአየር መንገዱ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል ጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መሆኑን ጠቁመው ስምምነቱ የተቀላጠፈ የደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የሁለትዮሽ ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆንም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮችና ሠራተኞች ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ ማረጋገጣቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡ 

አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ስምምነቱ እየጨመረ የመጣውን የመንገደኞችና የዕቃ ፍሰት ከግምት ውስጥ ያስገባ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡

ወደ ሀገር እንዳይገቡ ወይም ከሀገር እንዳይወጡ የተከለከሉና ገደብ የተጣለባቸውን ዕቃዎች በአግባቡ ለመቆጣጠር እና የትራንዚት ዕቃዎች በተቀመጠላቸው አሰራር እንዲስተናገዱ ስምምነቱ ፋይዳው የጎላ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም