የኢቢሲ አስደናቂ የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው -የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ - ኢዜአ አማርኛ
የኢቢሲ አስደናቂ የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው -የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) አስደናቂ የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ ምእራፍ የከፈተ መሆኑን የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ።
ኢቢሲ አዲስ ባስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ "በዘመን ጅረት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው የፎቶ ግራፍ አውደ- ርዕይና ሚዲያ ጋለሪ ዛሬ ተከፍቷል።
አውደ ርዕዩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የተለያዩ የሚዲያ ሃላፊዎች ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየት የሰጡ የሚዲያ ሃላፊዎች ኢቢሲ በሚዲያ ኢንዱስትሪ ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት ያለበትን የእድገት ደረጃ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ የደረሰበት ደረጃ ለሌሎች የሚዲያ ተቋምት በጎ የቅናት መንፈስንና ከፍ ብሎ ለመውጣት እድል ይሰጣል ብለዋል።
"እንደ ሚዲያ አመራር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የሚዲያ ተቋም በመገንባቷ ለሁላችንም ኩራት ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ የኢቢሲ አስደናቂ የለውጥ ሂደት ለኢትዮጵያ የሚዲያ ኢንዱስትሪ እድገት አዲስ ምእራፍ የከፈተና ሁላችንንም ያስደሰተ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ተቋሙ የአገር ሃብትና ኩራት ጭምር መሆኑን ጠቅሰው በሚዲያው ዕድገትና ከፍታ ውስጥ መረጃን ለህዝብ የማስተላለፍ ዕድልን የሚያሰፋ መሆኑንም ተናግረዋል።
በብሔራዊ ሚዲያ ደረጃ ትልልቅ ስራዎችን ሰርቶ መውጣት ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን ተሞክሮ ይሆናልም ነው ያሉት።
የኤንቢሲ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ፤ ኢቢሲ ታሪክን ጠብቆ በመዝለቅና ወደ ፊት ጠንካራ ሚዲያ ሆኖ ለመቀጠል እያደረገ ያለው አስደናቂ የለውጥ ሂደት አስደሳች ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ልማትና እድገት እንዲሁም የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሚዲያ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ግንባታ ላይ የሚሰሩ ሚዲያዎች ተጠናክረው መውጣት ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።
በፎቶ አውደርዕዩ ሚዲያው ያከናወናቸው ቀደምት ታሪኮችን የሚያሳይ በመሆኑ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።