ቀጥታ፡

በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያን የፋይናንስ አካታችነት ምጣኔ ወደ 70 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

ሃዋሳ ሰኔ 26/2015 (ኢዜአ)፡- በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያን የፋይናንስ አካታችነት ምጣኔ ወደ 70 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባንኮች የሀብት መጠን 2 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም ተናግረዋል።

የሲዳማ ባንክ በሃዋሳ ከተማ ከ500 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባው ሁለገብ ሕንጻ  ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፤ ሕንጻው በአራት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ፣የሲዳማ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ሀጢያ፣የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የባንኩ አመራሮች እና  የባንኩ ባለአክሲዮኖች ተገኝተዋል። 

ምክትል ገዥው በወቅቱ እንዳሉት  ሲዳማ ባንክ ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረገ የሪፎርም ስራ ከአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ ከተሸጋገሩ ባንኮች አንዱ ነው።

አነስተኛ ፋይናንስ ተቋማትን ወደ ባንክ የማሸጋገር ዓላማ የተቋማቱን እድገት፣የደንበኞቻቸውን ፍላጎት እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትን እውን ማድረግ ነው ብለዋል።

በ2015 በጀት ዓመት እስከ ሶስተኛው ሩብ የበጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ 31 ባንኮች የቅርንጫፎቻቸው ብዛት 10 ሺህ 968 መድረሱን ገልጸው የባንኮቹ የሀብት መጠንም 2 ነጥብ 9 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ጠቁመዋል።

"የባንክ ዘርፍ  በርካታ ተግዳሮቶችን አልፎ የመጣ ቢሆንም፣ በማያቋርጥ እድገት፣ትርፋማነትና አካታችነት ጉዞውን በስኬት ቀጥሏል" ነው ያሉት አቶ ሰለሞን።

በተለይ በወለድ ነጻ፣ በዲጂታል ክፍያና የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፍ በተከናወኑ የሪፎርም ስራዎች አማካኝነት በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሪፎርም ስራዎቹ ዘርፉን  ማዘመን ቢቻልም፤ የፋይናንስ አካታችነት 45 በመቶ ላይ መሆኑ ወደ ፊት  ብዙ  መስራትን እንደሚጠይቅ  አመላካች ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን የፋይናንስ አካታችነት እ.አ.አ በ2025 አሁን ካለበት 45 በመቶ  ወደ 70 በመቶ ለማድረስ መንግሥት አቅዶ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት።

የፋይናንስ አካታችነቱ የገጠሩን ማህበረሰብ፣ግብርናን፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የዲጂታል መታወቂያ፣የብድር መረጃና የተንቀሳቃሽ ዋስትና ስርዓት እንዲሁም የሞባይል ኔትወርክና ሌሎች መሰረተ ልማት ማሻሻያ በማድረግ አካታችነቱን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የባንኩ ስራ መጀመር የሕዝቡን ቁጠባ ባህል ለማሳደግ ፣የብድር አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።


 

የሲዳማ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ተቋሙ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በክልሉ  ከግማሽ ሚሊዮን ለሚበልጡ ወገኖች የፋይናንስ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


 

የሲዳማ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ሀጢያ በበኩላቸው ባንኩ ለደንበኞች የሚሰጠውን የብድር እና የቁጠባ አገልግሎትን ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ  እንዲሁም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሟላ የባንክ አገልግሎት በመጀመር ተደራሽነቱን ለማስፋትና ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ማቀዱን ገልጸዋል።

    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም