ቀጥታ፡

የምርምር ተቋማት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ ለአገራዊ እድገት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ)፦ የምርምር ተቋማት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ ለአገራዊ ልማትና እድገት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ውኃ አስተዳደር የልህቀት ማዕከል "በኢትዮጵያ የውኃ አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓትን" በተመለከተ አውደ ጥናት አኳሂዷል፡፡
 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ አበራ እንደሻው፤ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ ያለው የውኃና ኢነርጂ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረና የአሁኑን ጊዜ የማይመጥን መሆኑን ተናግረዋል።

ፖሊሲና ስትራቴጂው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚገድብ፤ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለመገምገም የሚያስቸግርና ሌሎችም ውስንነቶች ያሉበት መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም አሁን ያለውን የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂውን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት 48 በመቶ የንጹህ መጠጥ ውኃ ደግሞ 66 በመቶ ብቻ መሆኑን የገለጹት ልዩ አማካሪው፤ አገልግሎቱን ለማዘመን ፖሊሲውን ማሻሻል ግድ ብሏል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም መንግስት የማስተዳደርና የመቆጣጠር ሚናውን ወስዶ የግሉ ዘርፍ አገልግሎቱን በስፋት መስጠት በሚያስችል መንገድ ይቀረፃል ብለዋል፡፡

የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነዱ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ገልጸው፤ በሂደቱ የምርምር ተቋማት በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ በማቅረብ ፖሊሲ አውጭዎች ማገዝ አለባቸው ብለዋል፡፡

የምርምር ተቋማትም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ ለአገራዊ ልማትና እድገት የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የአፍሪካ ውኃ አስተዳደር የልህቀት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ፈለቀ ዘውገ፤ የኢትዮጵያ የውኃ ሃብት አጠቃቀም የሚመራበት መንገድ ውጤታማ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውኃ ሀብት አጠቃቀምና የአወጋገድ ሥርዓት ውስንነት እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የአሰራርና የፖሊሲ ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የልህቀት ማዕከሉ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጭምር የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የምርምር ሥራዎችን ለፖሊሲ ግብዓትነት መጠቀም የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የውኃ አቅርቦትና ኢንቫይሮመንታል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ኢሳያስ አለማየሁ፤ በኢትዮጵያ ብዙ ምርምሮች ቢደረጉም በአብዛኛው ጥቅም ላይ አለመዋላቸውን አንስተዋል።

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚያዘጋጀው ፖሊሲና ስትራቴጂ የምርምር ተቋማትን ተሳትፎ መጠየቁ የዳበረና ዘመኑን የዋጀ ሰነድ ለማዘጋጀት ያግዛል ብለዋል፡፡

የምርምር ተቋማት የሀገር ሀብት ፈሰስ አድርገውና ብዙ ደክመው የሚያገኙት የምርምር ውጤት በመሆኑ በውኃ ሀብት አስተዳደር ላይ ሊያሰራ የሚችል ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ኃይድሮ-ኢንቫይሮመንት ኢንጂነሪንግና ምርምር ማህበር ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ሁን ዌይ ሊ መንግስት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን የፖሊሲ ማሻሻያ እንደግፋለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም