የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገለፀ።
ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ፈተናውን ከኩረጃ ነፃ በሆነ መልኩ ለማከናወን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በፈተናው ዙሪያ ባዘጋጀው የጋራ የፀጥታ እቅድ ላይ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የፈተናዎች ኤጀንሲ፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራልና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ፖሊስ ያለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ያለጸጥታ ችግር እንዲከናወን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በአጠቃላይ የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ፖሊስ የተሻለ ተሞክሮ መውሰዱንም ነው ያብራሩት፡፡
ከዚህ አኳያ ያለፈው ዓመት ተሞክሮን መሰረት ባደረገ መልኩ ፈተናው ያለጸጥታ ችግር እንዲከናወን ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ፈተናው በስኬት እንዲከናወን የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መመሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ፤ ፈተናው በሰላም እንዲከናወን ፖሊስ ከትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ፈተናውን ሲጓጓዝ ተገቢውን እጀባ መስጠት፣ ፈተናው የሚሰጥባቸውን ተቋማት ሰላምና ድህንነት ማረጋገጥ እንዲሁም ሌሎች ሰላም የማስከበር ስራዎች ይከናወናሉ ነው ያሉት፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የትምህርት ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠቱን በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተው፤ ዘርፉን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ያለፈውን ዓመት ተሞክሮ በመቀመር በዘንድሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቡልቺሳ ሂርኮ፤ ፈተናውን ከኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ ለማከናወን ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የዝግጅት ስራዎች ቀደም ብለው መጀመራቸውም የተሻለ ስራ ለማከናወን እንደሚያግዝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸው፤ በክልሉ ፈተናው ያለ ምንም ችግር ከኩረጃ ነፃ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ጭምር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የተገኙ ግብዓቶችን በዝግጅት ምዕራፍ በማካተት ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ያሉ አመራሮች ፈተናውን በሰላም ለመስጠት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማተቤ ታፈረ ናቸው፡፡
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና 921 ሺህ 338 ተፈታኞች በ102 ፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን እንደሚወስዱ ይጠበቃል።