የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአንድነት ቤተ-መዛግብት፣ የዕፅዋት ማዕከልና የጤና ኤግዚቢሽንን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአንድነት ቤተ-መዛግብት፣ የዕፅዋት ማዕከልና የጤና ኤግዚቢሽንን ጎበኙ
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአንድነት ቤተ-መዛግብት፣ የዕፅዋት ማዕከልና የጤና ኤግዚቢሽንን ጎበኙ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ፤ በጉብኝቱ ላይ ለተሳተፉት የምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በገለፃቸውም የኢትዮጵያን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች እንዲሁም የታሪክ መዛግብትና ቅረሶችን በአግባቡ ጠብቆ የማቆየት፣ ትውልዱ እንዲያውቃቸው የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በጉብኝታቸው በአንድነት ፓርክ ስር የሚተዳደረውን እና በውስጡ ከ230 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎችን በተስማሚ ስርዓተ ምህዳር የያዘውን የዕፅዋት ማዕከል ተመለክተዋል።
የኢትዮጵያን የዕፅዋት ሀብት በአንድ በማሰባሰብ ለመጠበቅ የሚያስችል ማዕከል በመገንባቱም የምክር ቤቱ አባላት አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ ካሉ ከ6 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች መካከል ለምግብነት፣ ለመድሃኒት እና ሌላም ጠቀሜታ ያላቸውን ዕፅዋት በአንድ ማዕከል ማንበር መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
የዕፅዋት ሀብትን በአግባቡ ጠብቆና አውቆ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ትልቅ ክፍተት እንደነበር አስታውሰው፤ የአንድነት የዕፅዋት ማዕከል በራስ አቅም ተገንብቶ ለውጥ ማምጣቱ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ቀጣዩ የኢትዮጵያ የዕፅዋት የምርምር ማዕከል የመሆን አቅም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በመቀጠልም ከ140 ዓመታት በላይ የቆዩ የኢትዮጵያን የፅሁፍ ታሪኮች ሰንዶ የያዘውን ቤተመዛግብት ጎብኝተዋል።
በቤተመዛግብቱ ውስጥም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የወጣች የወረደችባቸውን ታሪካዊ ሁነቶች፣ የነገሥታቱን ውሳኔዎች፣ የኢትዮጵያውያንን የጦርነትና የድል ህያው ታሪኮች የያዘ መሆኑን አንስተዋል።
ቤተ መዛግብቱ የኢትዮጵያን የወል እውነቶች ሰንዶ በመያዝ ረገድ ፈር ቀዳጅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ አለፎ የአፍሪካ ታሪኮች ማዕከል የመሆን ዕድልም አለው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውን የጤና ኤግዚቢሽንም ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያ በባህላዊና በዘመናዊ የመድሃኒትና የህክምና አገልግሎት ወደተሻለ ምዕራፍ እየገባች መሆኗን፣ የጤና ኤከስቴንሽን ፕሮግራምን በመተግበርም ዘርፈ ብዙ ለውጥ መምጣቷን ዓይተናል ነው ያሉት።
በቀጣይ በጤናው መስክ ዓለም ከደረሰበት የህክምና ቴክኖሎጂ እድገት እኩል ለመራመድ ሀገር በቀል እውቀቶችን ከዘመናዊው ጋር አሰናስሎ መሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በቀጣይም ወደ ወከሉት ህዝብ ሲሄዱ በማዕከል ደራጀ የተሰሩትን በየክልሎች እንዲስፋፉ የማስገንዘብና ክትትል የማድረግ ስራ እንደሚያከናወኑ ገልጸዋል።
የለውጥ ሂደቱን በሁሉም መስክ በማፋጠን ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል።