ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ታሪክ ሰንዶ ለትውልድ የማስተላለፍ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው-አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር


አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን ታሪክን በድምጽና በምስል ሰንዶ ለትውልድ በማስተላለፍ ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን በመገንባት በኩል ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

አፈ-ጉባኤው ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ አዲስ ባስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ "በዘመን ጅረት" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀውን የፎቶ ግራፍ አውደ-ርዕይና ሚዲያ ጋለሪ በከፈቱበት ወቅት ነው።

አውደ-ርዕዩ ኢቢሲ በቴሌቭዥንና በሬዲዮ ቴክኖሎጂ ያለፈባቸውንና አሁን ያለበትን የስራ እንቅስቃሴ እንዲሁም በቀጣይ ያቀዳቸውን ተግባራት የሚያሳይ ነው።

አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከመገናኛ ብዙሃን የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆንም የተከፈተውን አውደ-ርዕይ ጎብኝተዋል።


 

ከጉብኝታቸው በኋላ ባደረጉት ንግግር ኢቢሲ ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ ህብረት ምስረታ፣ በህዳሴ ግድብ፣ በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች የምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ የስፖርትና የመዝናኛ መረጃዎችን ለህዝብ ሲያደርስ መቆየቱን አውስተዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅትም የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪው ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ ለመሄድ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

የተዘጋጀው የፎቶ ግራፍ አውደ-ርዕይና ሚዲያ ጋለሪ የጋራ ታሪክንና የወል እምነትን በድምጽና በምስል ክምችት የያዘ፤ ለምሁራን ማጣቀሻና  ለመጪው ትውልድ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

ተቋሙ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግልም በመንግስት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለትም አፈ-ጉባኤው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እድሪስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ታሪክ ያላት አገር እንደሆነች ገልጸዋል።


 

የተዘጋጀው አውደ ርዕይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ በታሪኩ ያለፈባቸውን ቴክኖሎጂዎች፣ የፖለቲካ አስተሳሰቦችና አሁን ያለበትን ማስገንዘብ የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተለያዩ ዘመናት ትውልድ ሰርቶ ያለፋቸውን ታሪኮች ሰንዶ በማስቀመጥና እውቅና በመስጠት ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ታሪክ ያላት አገር እንደመሆኗ ሁሉም መገናኛ ብዙሃን በሃሳብና በሃብት በቅንጅት በመስራት አንድነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አንድነትን ለመሸርሸር በዲጂታል ሚዲያ የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎችን መመከትና ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለመገናኛ ብዙሃን መረጃን ከመስጠት አንፃር የመንግስትም ሆነ ሌሎች ተቋማት ግዴታ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው ፤ የአውደ-ርዕዩ ዋና ዓላማ የሚዲያው ኢንዱስትሪ ያለፈባቸውን ታሪኮች ለትውልድ ማስተላለፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአውደ-ርዕዩ መክፈቻ ላይ የተገኙ የሚዲያ ሃላፊዎች በኩላቸው፤ ኢቢሲ በዘመናዊ ስቱዲዮ፣ በምስል ክምችት አያያዝና ሌሎች መስኮች እያከናወነ ያለው ተግባር እንደ ትምህርት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ኢቢሲ ወደ ትልቅ ምዕራፍ እየገሰገሰ ያለ የሚዲያ ተቋም መሆኑን የሚያረጋግጥ ስራ ማየታቸውን ገልጸዋል።

ይህም የኢቢሲ ብቻ ሳይሆን የአገር ሃብት በመሆኑ በሚዲያው ዕድገትና ከፍታ ውስጥ መረጃን ለህዝብ የማስተላለፍ ዕድልን የሚያሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኤን ቢ ሲ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ከበደ ኢትዮጵያዊ ማንነት በመገንባት ሂደት ለይዘት ስራ ትኩረት መስጠት አለብን ብለዋል።

የፎቶ ግራፍ አውደ-ርዕይና ሚዲያ ጋለሪ መክፈቻው ላይ የአገር ውስጥ፣ የግልና የህዝብ የሚዲያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም