በምክክር አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን- የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን- የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር በምክክር አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ለማካሄድ የተሳታፊዎች ልየታ እና የመወያያ አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ስራ በማከናወን ላይ እንዳለ ይታወቃል።
በድሬደዋ፣ በሀረር፣ በሲዳማ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታና አጀንዳ የመቀበል ስራ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ በተሳታፊዎች መረጣ እና በአጀንዳ መሰብሰብ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ሰባት ተባባሪ አባላትንም ለይቷል።
ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተጠቃሽ ናቸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ምክክርና ውይይቶችን ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የመወያያ አጀንዳዎች ተለይተው ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ቀርበው ውጤታማ ውይይትና መግባባት እንዲፈጠር የሁላችንም ትብብር ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር በምክክር አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ጉባኤው በሀገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል ።
የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር የተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ የመሰብሰብ ስራ ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርን ውጤታማ በማድረግ የተሻለች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሁሉም የሀይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የእድሮች ማህበራት ጥምረት፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የወረዳ (ልዩ ወረዳ) አስተዳደር ተወካዮች የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት ናቸው።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚል በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወሳል።