ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ገለጸች 


አዲስ አበባ ሰኔ 26/2015 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ (UNMISS) ድጋፍ ማድረጓን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከዩኤንሚስ(UNMISS) ምክትል ኃላፊ እና ከተመድ የደቡብ ሱዳን ምክትል ልዩ ተወካይ ጉዋንግ ኮንግ ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በቀጣናው ባለው የሰላም እና ደህንነት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

ጉዋንግ ኮንግ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተወጣች ያለው ወሳኝ ሚና እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ለዩኤንሚስ እያደረጉት ያለውን ትልቅ አበርክቶ አድንቀዋል።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው መረጋጋት እንዲሰፍን አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዩኤንሚስ ለሚያከናውናቸው ስራዎች በቀጣይ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ(ዩኤንሚስ) በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ውሳኔ የተቋቋመው እ.አ.አ በ2011 ነው።

የተልዕኮው አላማ በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አማካኝነት አገሪቷ ዳግም ወደ እርስ በእርስ ጦርነት እንዳትመለስ መከላከል፣ ጠንካራ ሰላም መገንባት እንዲሁም ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ነጻ ምርጫ እንዲካሄድ ድጋፍ ማድረግ ናቸው።

ኢትዮጵያ ለዩኤንሚስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ካበረከቱ አገራት መካከል በዋናነት ትጠቀሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም