ቀጥታ፡

ጅማ እና ጅንካ ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን  ለመስጠት  ዝግጅት ማድረጋቸውን ገለጹ

ጅማ /ጅንካ ሰኔ 26/2015(ኢዜአ):- የጅማ እና ጅንካ ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን ለመስጠት   ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ።

ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚጀመረው የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 8 2015 ይሰጣል።

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሰለጠኑ 4 ሺህ 387 ተማሪዎች  ፈተናውን ለመስጠት መዘጋጀቱን ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ እንዳሉት ፈተናው የመጀመሪያው በመሆኑ ተማሪዎች በቂ ጥናት እና ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችል የሞዴል ፈተና ወጥቶላቸው እንዲፈተኑ ተደርጓል።

ለተማሪዎች አጋዥ የማጠናከሪያ ትምህርቶች እየተሰጠ እንደሚገኝ እና ተማሪዎች ፈተናውን በብቃት ተዘጋጅተው እንዲፈተኑ አስፈላጊው ድጋፍ እየተረገላቸው ይገኛል ብለዋል።

የመውጫ ፈተናው  በበይነ መረብ የሚሰጥ በመሆኑ በዩኒቨርስቲው ባሉ የኮምፒዩተር ቤተ ሙከራዎች በአጠቃላይ 2 ሺህ 113 ኮምፒዩተሮች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

በፈተናው ወቅት የኃይል መቆራረጥ  ችግር እንዳያጋጥም አማራጭ ኃይል ለመጠቀም ዝግጅት መደረጉንና  ከኢንተርኔት ሰርቨር ዝግጅት ጋር በተያያዘም ከኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን ነው ዶክተር ታደሰ ያስረዱት። 

በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚፈተኑ ተማሪዎች በበኩላቸው ፈተናውን ለመውሰድ በአግባቡ መዘጋጀታቸውንና ሞዴልን ጨምሮ የወሰዷቸው የተለያዩ ፈተናዎች እንዲሁም የማጠናከሪያ ትምህርቶች ለዝግጅታቸው እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጅንካ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 255 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን እንደሚወስዱ አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የአካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ተወካይ ወይዘሮ ፋጡማ  አራጋው በማካካሻ ትምህርቶች ተማሪዎችን የማብቃትና በፈተና መተግበሪያዎች ላይ  ስልጠና በመስጠት ተማሪዎቹን የማዘጋጀት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገም እንዲረዳቸው የሞዴል ፈተናዎችን ዩኒቨርስቲው በራሱ ባበለፀገው ሶፍትዌር አማካኝነት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው ይህም ተማሪዎቹ በእውቀት እና በስነ-ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል።

ፈተናው በበይነ-መረብ  የሚሰጥ እንደ መሆኑ በፈተናው ወቅት የኢንተርኔት እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ እንዳይኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቂ ዝግጅት ተደርጓል ነው ያሉት።


 

በዩኒቨርሲቲው ፈተና የሚውስዱ ተማሪዎች በበኩላቸው ዘንድሮ የሚሰጠውን የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና በላቀ ውጤት ለማለፍ በእውቀት እና በስነ ልቦና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የትክክለኛ ተፈታኞችን ቁጥር እንዲያጣራ በማድረግ÷ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 95 ሺህ 755 እንዲሁም ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች 74 ሺህ 776 የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ለመውጫ ፈተና እንደሚቀመጡ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም