በሀረሪ እና ጋምቤላ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ እና ጋምቤላ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ ነው
ሐረር/ጋምቤላ ሰኔ 26/2015 (ኢዜአ) በሀረሪ እና ጋምቤላ ክልሎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ መሆኑን የየክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ገለጹ።
በሀረሪ ክልል የ8ኛ ክፍል ፈተና ዛሬ ጠዋት ጀምሮ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አብይ አበበ ናቸው፡፡
ፈተናውን በቤተልሄም 1ኛ ደርጃ ትምህርት ቤት ያስጀመሩት ምክትል ሃላፊው እንደተናገሩት ለፈተናው አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በክልሉ ባጠቃላይ 17 የፈተና ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሲሆን 4 ሺህ 600 ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ፈተናው ባሉት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጨምሮ ተማሪዎችን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለፈተና እንዲቀመጡ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
ትምህርት ቢሮው ተማሪዎችን ለፈተና ለማብቃት እና ውጤትን ለማሻሻል በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
በተለይም የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና ለማብቃት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ሙሉ ቀን በትምህርት ቤቶች የማጠናከርያ ትምህርት ሲሰጥ መቆቱን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በጋምቤላ ክልል ከ22 ሺህ 550 ለሚበልጡ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ዛሬ እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው የስርዓተ ትምህርት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡኩኝ ኡቡያ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የ8ኛ ክፍል ፈተናው እየተሰጠ ያለው በክልሉ በሚገኙ 205 ትምህርት ቤቶች ነው ።
ፈተናውን እየወሰዱ ከሚገኙት 22 ሺህ 551 ተማሪዎች መካከል ዘጠኝ ሺህ 746ቱ ሴቶች መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ለሶስት ቀናት የሚቆየው የፈተና ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊና ከኩረጃ ነፃ ለማድረግ በየፈተና ጣቢያው አስፈላጊው የጸጥታ አካላት መመደቡን ገልጸዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከልና ሰላም ማስከበር ዋና የስራ ሂደት ኮማንደር ቱዎል ኡኮት በበኩላቸው በክልሉ እየተሰጠ ያለው የ8ኛ ክፍል ፈተና ያለንም ችግር እንዲጠናቀቅ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ከትናንት ጀምሮ በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች አስፈላጊውን የፖሊስ ኃይል በመመደብ ለፈተናው ሂደቱ አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።