ቀጥታ፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገው ንቅናቄ ተወዳዳሪ አገር የመገንባት ሂደት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊሳተፍ ይገባል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2015 (ኢዜአ) የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገው ንቅናቄ ተወዳዳሪ አገር የመገንባት ሂደት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊሳተፍ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ አገር አቀፉን የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄ መርሃ-ግብር በዛሬው እለት በይፋ አስጀምረዋል።

በንቅናቄው የኀብረተሰቡን ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ የሚሰራ ይሆናል።

በዚህም በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ከ50 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እንደሚሰራም ነው የተገለጸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ትምህርትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር የሚሆን መሰረተ ልማት በማሟላት በኩል በብዙ ወደ ኋላ መቅረታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም በፍጥነት እየተለዋወጠ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም አውድ ውስጥ ተፎካካሪ አገር መገንባት የሚቻለው ትምህርት ላይ በመስራት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ አኳያ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት የተሻሉ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄው በትብብር ለትውልድ የሚሆን ተግባር በማከናወን የኢትዮጵያን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የእናንተን ድጋፍ ይሻሉ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል የሚደረገውን ንቅናቄ ማገዝ አለብን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆን ለትምህርት ጥራት መጓደል ተጠቃሽ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በአገር አቀፍ ደረጃ ከ86 በመቶ በላይ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ የሆኑ መሰረተ ልማቶች እንዳልተሟሉላቸው ነው የተናገሩት፡፡

ይህም በተለያዩ መስኮች አገራቸውን የማገዝ  አቅም ያላቸው ዜጎች እድሉን እንዳያገኙ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ችግር በመንግስት ብቻ ለመፍታት ቢሞከር ከ30 ዓመታት በላይ እንደሚወስድ ጠቅሰው፤ በመሆኑም ኀብረተሰብን ያሳተፈ ንቅናቄ መፍጠር አስፈልጓል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከሚሳተፉ ስመ-ጥር ግለሰቦች መካከል አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በርካታ ህጻናት አሁንም በዳስ እንደሚማሩ ተናግሯል፡፡

ይህ እንዲቀጥል መፍቀድ አይገባም ያለው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ትምህርት ላይ መስራት የተሻለችና ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን መገንባት መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚህ አኳያ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል የተጀመረውን ንቅናቄ ማገዝ የህሊና ደስታ የሚሰጥ በጎ ተግባር መሆኑን ተናግሯል፡፡

አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ በበኩሉ፤ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች 30 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶችን መገንባቱን ገልጿል፡፡

በትምህርት ቤቶች ግንባታ ሂደት ማህበረሰብን በባለቤትነት ማሳተፍ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ከገነባቸው ትምህርት ቤቶች ያገኘውን ልምድ አካፍሏል፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም