ማህበሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለስድስት ወለል ህንጻ ዛሬ አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለስድስት ወለል ህንጻ ዛሬ አስመረቀ
አምቦ ሰኔ 25/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለስድስት ወለል ህንጻ ዛሬ አስመርቋል፡፡
የቀይ መስቀል ማህበርን ተልእኮ ለማሳካት አቅምን ማጠናከርና ከውጭ እርዳታ ጠባቂነት መላቀቅ አስፈላጊ መሆኑን የማህበሩ የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለገሰ ለቺሳ ገልጸዋል፡፡
አቶ ለገሰ ለቺሳ ህንጻውን ሲያስመርቁ እንዳሉት የተመረቀው እንጻ የተለያዩ ገቢዎችን በማስገኘት ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ ተግባራት ላይ ይውላል፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከተመሰረተበት 1996ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ሰብአዊ እና የልማት ተግባራትን ሲያካሂድ የነበረና በማካሄድ ላይ ያለ ድርጅት መሆኑንም ተናግረዋል።
የቀይ መስቀል ማህበርን ተልእኮ ለማሳካት አቅምን ማጠናከር እና ከውጭ ሀገር እርዳታ ጠባቂነት መላቀቅ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ እራሳችንን ለመቻል ገቢ ማስገኛ ህንጻ በመገንባት ተጠቃሚ ሆነናልም ብለዋል፡፡
ማህበሩ በዞኑ 6 ቅርንጫፎች እንዳለው ገልጸው በቅርንጫፎቹ አማካኝነት በዞኑ ውስጥ አምቦ ከተማን ጨምሮ በ22 ወረዳዎች በበጎ ፈቃደኞች በመታገዝ መጠነ ሰፊ ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ኖኖ፣ ጀልዱ፣ ጅባት፣ አቡና ግንደበረት፣ ኤጄሬ፣ ኤጀርሰ ለፎ ወረዳዎችና አምቦ ከተማ ለሚገኙ ወገኖች ያለፈው አመትና በዚህ ዓመት 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል፡፡
በዞኑ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለማዳረስ በተደረገ ጥረት በ18 ወረዳዎች 27 የምንጭ ውሃ በማጎልበት ለየወረዳዎቹ ውሃ ጽህፈት ቤቶች ማስረከቡንም ተናግረዋል፡፡
የዞኑ ህዝብም በማህበሩ በኩል የተገነቡ መሰረት ልማቶችን በአግባቡ መጠቀምና መጠበቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወርቅነህ መኮንን እንደተናገሩት በዛሬው እለት የተመረቀው ህንጻ በ700 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ከህንጻው ኪራይ በዓመት 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡
የህንጸው ግንባታ የተከናወነውም የማህበሩ አባላት በየአመቱ በሚያሰባስቡት መዋጮና በህብረተሰብ ተሳትፎ ነው ብለዋል፡፡
ለህንጻው ግንባታ 20 ሚሊየን 53 ሺህ 681 ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህም የተገኘው በህብረተሰብ ተሳትፎ መሆኑን በማከል፡፡
የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ በበኩላቸው ማህበሩ ለህብረተሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በአምቦ ከተማ የተገነባው ባለ ስድስት ወለል ህንጻ ለከተማውና ለዞኑ ህብረተሰብ ትልቅ ነገር በመሆኑ እንክብካቤ እና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የምዕራብ ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 180ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን በአመት ከአባላቱ በአማካይ 3 ሚሊየን 200 ሺህ ብር ያሰባስባል፡፡