ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ወረዳ እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ከተማ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

ሞያሌ/ሐረር ሰኔ 25/2015 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ወረዳ እና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ከተማ የተገነቡ የመስኖና ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተመረቁ ለአገልግሎት ክፍት እየሆኑ ይገኛሉ።

በዚህም በሞያሌ ወረዳ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን የቡርቁቄ መስኖ ግድብ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የመስኖ ግድብ ድርቅ በሚከሰትበት ቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ ሲሆን ግድቡ ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

ግድቡ 53 ሄክታር መሬት የሚያለማ ሲሆን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚይዝ እንደሆነም ታውቋል።
 

ግድቡ በሞያሌ ወረዳ ቡርቁቄ ቀበሌ ያሉትን አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ግንባታው አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት ውሃ ይዞ ለልማት ዝግጁ ሆኗል።

በተመሳሳይ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ ከተማ 38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው 16 የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት የክልሉ መንግስት ለልማት ፕሮጀክቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመሥጠት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

አቶ ዳንኤል ቸርነት ፕሮጀክቶቹን የመረቁት ከምስራቅ ሀረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያለው ታከለ ጋር በመሆን መሆኑም ተገልጿል።

የክልሉ መንግስት ፕሮጀክቶችን በብዛትና በጥራት ለማከናወን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ነው አቶ ዳንኤል ጨምረው የገለጹት።

የባቢሌ ከተማ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በአብሮነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ጠቁመው፤ በከተማው ያለውን የአንድነትና አብሮነት እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባልም ብለዋል።

የባቢሌ ከተማ የምትታወቅበትን የባቢሌ ድንጋይ አልምቶ ለቱሪዝም መስህብነት በመጠቀም ለትውልድ ለማስተላለፍ ትኩረት ተሠጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም እንዲሁ።

የምስራቅ ሀረርጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አያሌው ታከለ በበኩላቸው በበጀት አመቱ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን በ 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወጪ 386 ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ልዩ ትኩረት በመስጠት ፕሮጀክቶችን በብዛት እና በጥራት በመገንባት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የባቢሌ ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር ገና በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት ፕሮጀክቶች በ2015 በጀት አመት የተከናወኑ 16 ፕሮጀክቶች መሆናቸውን በመጠቆም 38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 150 ሜትር የውሃ መውረጃ የድጋፍ ግንብ እና ዲች፣ የገበያ ማዕከል፣ 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እና ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የእናቶች ወሊድ ማእከል ይገኙበታል ብለዋል።

አርሶ አደር አሊ አቢብ በበኩላቸው ከአሁን ቀደም በአካባቢያቸው የሚያልፈው ጎርፍ በማሳቸው ላይ ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ማስከተሉን በማስታወስ በአካባቢው የተገነባው የድጋፍ ግንብ በማሳቸው ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነሱን ገልጸዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ሀዋ በከር በበኩላቸው የተገነባው የገበያ ማዕከል የመሸጫ ቦታ ችግራቸውን እንደሚቀርፍላቸው ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ለ 1 ሺህ 500 ዜጎች ጊዚያዊና ቋሚ የስራ እድል የፈጠሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም