በዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን ነው-የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2015(ኢዜአ)፦ በሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን ነው ሲሉ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ማስታወቁ ይታወሳል።

የመውጫ ፈተናው ተማሪዎች በተማሩባቸውና በሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች ብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የመውጫ ፈተናው በኦንላይን ለሁሉም የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ ሚኒስቴሩም ይህን የሚመጥን ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ተማሪዎች ለፈተናው እያደረጉት ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተፈታኝ ተማሪዎችን አነጋግሯል።

ተፈታኝ ተማሪዎቹ እንዳሉት በሐምሌ ወር ለሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን ለመውሰድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ነው።

ተማሪ እድላዊት አለሙ በመጪው ሃምሌ ወር ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና አስፈላጊውን የጥናት ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ገልፃለች።

በዝግጅቷም ፈተናውን በውጤት በመቋጨት ለቤተሰቧም ሆነ ለእራሷ ደስታና ስኬትን ለማምጣት የጥናት ዝግጅትና የማካካሻ ትምህርት እየወሰደች እንደምትገኝ ተናግራለች።

ሌላኛው ተፈታኝ ተማሪ በኃይሉ እንዳለው፤ የመውጫ ፈተናውን በውጤት ለመቋጨት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የመውጫ ፈተናው በዩንቨርሲቲ ቆይታዬ ያገኘሁትን እውቀት ለመለካትም ያግዘኛል ሲል ነው አስተያየት የሰጠው።

ለፈተናው ከሚያደርጉት ዝግጅት ጎን ለጎን የፈተና አሰጣጥ መረጃዎቸን በበቂ ሁኔታ ለተማሪዎች ማድረስ ይገባል ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ።

ሌላኛዋ ተፈታኝ ተማሪ እድላዊት ግሩም በበኩሏ የመውጫ ፈተናውን በተሻለ ውጤት ለመቋጨት ተማሪዎች ጥናት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተናግራለች።

የዩኒቨርሲቲው የስነ-ልቦና ባለሙያና መምህር ዶክተር ከበደ ትርፌሳ፤ የመውጫ ፈተናውን በውጤት ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በዩንቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀሪ ጥቂት ቀናት ውስጥም ተማሪዎች ተረጋግተው በማጥናት ዝግጅት አድርገው የሚሰጡ የመውጫ ፈተናዎችን ተረጋግተው መውሰድ እንደሚኖርባቸውም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም