የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሐ-ግብሩ መሰረት ሀዲያ ሆሳዕና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ ዘጠኝ ላይ ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሀዲያ ሆሳዕና በ40 ነጥብ 8ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ60 ነጥብ የሊጉን የመጀመሪያ ደረጃ ይዟል።
ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በተመሳሳይ በአንዱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በዛሬው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ለ16ኛ ጊዜ ማንሳቱን ያረጋግጣል።
በ29ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታ በባህር ዳር ከተማ እና ሃዋሳ ከተማ መካከል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
በደረጃ ሰንጠረዡ ባህር ዳር ከተማ በ54 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ41 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባህር ዳር በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ሃዋሳ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ማረጋገጡ ይታወቃል።
በተያያዘም ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተደረጉ የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ለገጣፎ ለገዳዲ ሲዳማ ቡናን 3 ለ 2 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና መቻልን 2 ለ 1 አሸንፈዋል።