ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሙያዊ ስነምግባርንና ብቃትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ ሰኔ 24 /2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሙያዊ ስነምግባርንና ብቃትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2015 በጀት ዓመት ለተመዘገቡ ስኬቶች የላቀ አስተዋፅአ ለነበራቸው አመራሮች፣ አባላትና ባለድርሻ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሐግብር በሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል።

በመርሐግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል እና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል እና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት፤ በሪፎርሙ በተሰራው ጠንካራ ስራ አሁን ላይ የወንጀል መከላከል አቅም ማደግ መቻሉን ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ አሁን ላይ በቴክኖሎጂ አቅም፣ በትጥቅ እና በሰው ሃይል ራሱን አደራጅቶ የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅና ወንጀልን ለመከላከል ስምሪት ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከዚህም ባለፈ የወንጀል ምርመራ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳደጉ ለውጦችን በማድረግ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።

ከለውጡ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፀምበት የነበረው የምርምራ ማዕከል መዘጋቱንም ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ፖሊሳዊ የምርመራ ሰነ-ምግባር መርህን በመጠበቅ ምርመራ የሚያካሂድ ጠንካራ ተቋም መገንባቱን ተናግረዋል።

የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያው ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ የድንበር ዘለል ወንጀሎች የምርመራ ተቋም እንዲሆን የመምሪያው አመራርና አባላት በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሙያዊ ስነምግባርንና ብቃትን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ስራ በቁርጠኝነት እየተተገበረ መሆኑን በማንሳት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።


 

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርምራ ጠቅላይ መምሪያ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ በህዝብና ሀገር ላይ የተፈጸሙ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመርመር አጥፊዎችን ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን አብራርተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ለጥፋት የታቀዱ ትልልቅ ወንጀሎች ከመፈጸማቸው አስቀድሞ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ማክሸፍ መቻሉንም ተናግረዋል።

በጠቅላይ መምሪያው የሚደረጉ የወንጀል ምርምራ ተግባራት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበሩና የፖሊስ የምርመራ ስነ-ምግባር መርህን የተከተሉ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሚካሔዱ የምርመራ ስራዎች በተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊት ላይ ብቻ ያተኮሩ፤ ህግን መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ይሕም የተቋሙን የለውጥ ስራ ውጤታማነት ያመላክታል ብለዋል።

ጠቅላይ መምሪያው ባከናወነው የሪፎርም ስራ ዓለም አቀፍ የፖሊስ የምርመራ ደረጃን በማሟላት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርመራ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዘመናዊ የቃል መቀበያ ቢሮዎች፣ ተጠርጣሪዎች ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር በነጻነት የሚመካከሩበት ስፍራ፣ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ማረፊያ እና መጠየቂያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

የተጠርጣሪ ምዝገባና አስተዳደር መረጃዎች ሙሉ በሙሉ በኮምፒውተር የተደራጁ መሆኑንም አንስተዋል።

ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ራዕይ በመሰነቅም ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።


 

እውቅና ከተበረከተላቸው ተሸላሚዎች መካከል ኮማንደር በለጠ ጌታቸው እና ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፖሊስ የወንጀል ምርምራ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀይሯል ብለዋል።

በዚህም አሁን ላይ የወንጀል ምርምራ ተግባር በዲሲፕሊንና በፖሊሳዊ ስነምግባር እየተተገበረ መሆኑንም ጠቅሰው፤ እነሱም የምርመራ ሂደቱን ሙያዊ አካሄድ የማጠናከር ስራን እንደሚያግዙ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም