ቀጥታ፡

አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የአስተዳደሩ ፖሊስ  የጀመረውን አበረታች ስራ ማጠናከር አለበት -ከንቲባ ከድር  ጁሃር 

ድሬዳዋ ሰኔ 24 /2015 (ኢዜአ) ፡-  የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ አስተማማኝ በማድረግ የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የአስተዳደሩ ፖሊስ እያከናወናቸው ያሉት ተግባራት ማጠናከር እንዳለበት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር  አሳሰቡ። 

ከንቲባው  በድሬዳዋ ስታዲየም ለ13ኛ ጊዜ  ዛሬ ለተመረቁት የድሬዳዋ ሰልጣኝ ምልምል ፖሊሶች ባስተላለፉት መመሪያ፤ ተመራቂዎች የአስተዳደሩን ነዋሪዎች  በእኩልነትና በታማኝነት በማገልገል ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። 

በቀጣይ  የህዝቡና የአስተዳደሩን ብሎም የሀገርን ሰላም ፣ደህንነትና የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ ፤የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከነዋሪው ጋር ተቀናጅቶ የድሬዳዋን አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት የጀመረውን አበረታች ስራ ማጠናከር አለበት።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ  እንደተናገሩት ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተቋሙ ባካሄደው የሪፎርም ስራዎች የተጣለበትን ሰላምን የማስፈንና የነዋሪውን ደህንነት የመጠበቅ ስራ አስተማማኝ ደረጃ ላይ አድርሶታል።

በተለይ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርና አደረጃጀት በመፍጠር እንዲሁም ብቁና ታታሪ የሰው ኃይል በማፍራት  የተከናወኑ ስራዎች ድሬዳዋ ምቹ የመኖሪያ እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዛሬው ተመራቂዎችም የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የቀሰምነው የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ትምህርት የዜጎችን፣የድሬዳዋ እና የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለመጠበቅ ያግዘናል ያላችው  ተመራቂ ፖሊስ ኮንስታብል ቤዛ ወንድሙ  ናት።


 

ሌላው በስልጠናው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የተመረቀው የዕለቱ ኮኮብ ተሸላሚ  ኮንስታብል አቤነዘር አሰፋ፤ ለአራት ተከታታይ ወራት የቀሰምነው ዕውቀት ሀገርንና ወገን በታማኝነት ለማገልገል የሚያስችለንን ስብዕና ለመላበስ  አብቅቶናል ብሏል።

በቀጣይ ለሀገርና ህዝብን ህይወትን በመስጠት ጭምር በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።


 

ከንቲባ ከድር ጁሃር  በስልጠናው ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አባላት የተዘጋጀውን ሽልማት አበርክተዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ  የድሬዳዋ አስተዳደር የካቤኔ አባላት፤ የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ጽህፈት ቤት አመራሮች ፤ የሐረሪ  ክልል እና የኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን የፖሊስ ኮሚሽነሮች ፣ የተመራቂ ቤተሰቦችና ሌሎችም አካላት ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም