የተመረቁ ወጣቶች የፈጠራ እና የስራ ባህልን በማጎልበት ተግተው መስራት አለባቸው - አቶ መስፍን መላኩ - ኢዜአ አማርኛ
የተመረቁ ወጣቶች የፈጠራ እና የስራ ባህልን በማጎልበት ተግተው መስራት አለባቸው - አቶ መስፍን መላኩ
ጅማ ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በቴክኒክ እና ሙያ የተመረቁ ወጣቶች የፈጠራ እና የስራ ባህልን በማጎልበት ተግተው መስራት እንደሚገባቸው በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የክልሉ ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ አሳሰቡ።
በክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከ26 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ወስደው መመረቃቸው ተመላክቷል።
በጅማ ዞን እና በጅማ ከተማ 26 ቴክኒክና ሙያ ተቋማት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የወሰዱ 3 ሺህ 508 ወጣቶች ተመርቀዋል።
በምረቃ መርሐ-ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ክላስተር አስተባባሪ አቶ መስፍን መላኩ በክልሉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ፈጠራን የሚያሳድጉ የተለያዩ ድጋፎች ለወጣቶች እየተሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከስልጠናና ትምህርት ጎን ለጎን ፈጠራን በማበረታታት የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ወጣቶች ከምንም በላይ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የፈጠራ እና የስራ ባህልን በማጎልበት ተግተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው የተመረቁ ወጣቶች ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የሰው ኃይል አቅምን በእውቀት እና በክህሎት በማጎልበት ለወጣቱ የስራ እድልን ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በዚህ አመት ከ26 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ወስደው በማጠናቀቅ የተመረቁ መሆኑን ገልጸው ወጣቶቹን ወደ ስራ ለማስገባት ይሰራል ብለዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው በዞኑ ያሉ ሁሉንም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችን በመደገፍ የበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው የተመረቁ ወጣቶች በበኩላቸው ባገኙት እውቀት መሰረት ራሳቸውን ለመለወጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ስራ ለመጀመር የሚያስፈልጉት ግብአቶችም እንደሚሟሉላቸው ጠይቀዋል።