በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ መልክዓ ምድር ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል

ካራት ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ ዓለም አቀፍ መልክዓ ምድር እየደረሰበት ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ  የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር ዓለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር  ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ዘጠነኛው የኮንሶ ባህል፣ታሪክና ቅርስ ሲምፖዚየም በካራት ከተማ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።

የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ገረመው ጌቱ ለኢዜአ እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበችው የኮንሶ መልክዓ ምድር  በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰበት ይገኛል። 


 

ለዚህም ከዘመናዊነት ጋር በተያያዘ የመጣ የቤቶች ግንባታ መበራከት፣በቅንጅት ማነስና ባለመናበብ የሚደረግ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ዋነኞቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሀገር በቀል ዕውቀትን ለመውረስ ያለው ዝቅተኛ አመለካከት እንዲሁም የግንዛቤ እጥረትም እንዲሁ።

እየደረሰበት ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተቀናጀ ጥረት እንዲሚያስፈልግ ያስታወቁት አስተባባሪው ሲምፖዚየሙ በቅርሶቹ አያያዝና አጠባበቅ ከገጠማቸው ችግር በሚወጡበት መንገድ ያተኮረ የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር እንደሚመክር ተናግረዋል።

ጽህፈት ቤቱ ምሁራን፣አመራር አካላትንና ህዝብን በማሳተፍ ችግሮቹን ለማቃለል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው፤ ''አባቶቻችን ጠብቀው በዓለም አቀፍ ያስተዋወቁትን ቅርስ ጠብቀን ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን'' ብለዋል።

ለዚህም በቅርሶቹ አያያዝና ጥበቃ ላይ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኮንሶ ዓለም አቀፍ መልክዓ ምድርን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ቅርሶቹ ባሉበት አካባቢ የሚካሄዱ የመሠረተ ልማተ ተቋማት ግንባታ ቅርሶችን በማይጎዳና በማይነካ መልኩ እንዲከናወኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ጥረት እንደሚደረግም አብራርተዋል።   

በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ገመቹ ገንፈ በሰጡት አስተያየት፤ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው ሀብት በእንክብካቤ ጉድለት አደጋ ላይ መውደቁን እየታዘቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

''ኮንሶ የአየር ጸባዩና መሬቱ ለእርሻ ምቹ ባይሆንም፤ አባቶች በእርከንና በባህላዊ ኩሬ ውሃ በማቆር ተፈጥሮን ተቋቁመን የምንኖርበትን ዘዴ አስተምረውናል'' ብለዋል።

አባቶች የተለያዩ ችግሮች ተቋቁመው በአንድነት ተሰባስበው የሚኖርባቸው ባህላዊ መንደሮችን መስርተው ለትውልድ ማሸጋገራቸውን ጠቅሰው፤ የአሁኑ ትውልድም ይህን የማቆየት አደራ እንዳለበት አመልክተዋል።

''ቅርሱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፉ ኃላፊነት የእኛ ጉዳይ ነው ፤ ለቅርሶቹ እንክብካቤ በማድረግ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባናል'' ብለዋል።

የኮንሶ ዓለም አቀፍ መልክዓ ምድር በ23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና በውስጡ በርካታ ቅርሶችን የያዘ ሲሆን፤ የእርሻ እርከኖች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ባህላዊ ኩሬዎችና ባህላዊ መንደሮች እንዳሉትም ተገልጿል።

ቅርሱን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) እንዳስመዘገበችው መረጃዎች ያመለክታሉ።  

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም