ቀጥታ፡

በአማራ ክልል   ለሚሰጠው የ8ኛ ክፍል ፈተና በቂ ዝግጅት ተደርጓል

ባህር ዳር ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል  ለሚሰጠው  የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በቂ  ዝግጅት መደረጉን የክልሉ  ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የትምህርት ምዘናና የጥናት ቡድን መሪ አቶ ዝጋለ ማሩ ለኢዜአ እንደገለጹት ለ347 ሺህ 966 ተማሪዎች ፈተናው ከኩረጃና ከስርቆት ነፃ ሆኖ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት  ተደርጓል።

በክልሉ የ8ኛ ክፍል ፈተና በሚሰጥባቸው 5ሺህ 657 ትምህርት ቤቶች ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅም በየደረጃው የፈተና ግብረ ኃይል መቋቋሙን፣ 4ሺህ 432 የጣቢያ ኃላፊዎች፣ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሱፐርቫይዘሮች እና ከ11 ሺህ 690 በላይ ፈታኝ መምህራን መመደባቸውን ተናግረዋል።

ፈተናውን በወቅቱ በማሳተም ለሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች እንዲደርስ መደረጉን ገልጸው፤ የፈተና  አስፈጻሚዎችና  የጸጥታ አካላት ከነገ ጀምሮ ወደ ተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች እንደሚሄዱም ገልጸዋል።

ከፀጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ፈተናው ከማጓጓዝ ጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያግዙ  የፖሊስና ሚሊሻ አባላት እንዲመደቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ 187 ዐይነ-ስውራን ተማሪዎች ፈተናውን በአግባቡ እንዲወስዱ የሚያስችሉ አንባቢዎች መመደባቸውን አቶ ዝጋለ አስረድተዋል።

ቡድን መሪው አክለውም ቀደም ሲል የ7ኛ ክፍል ትምህርትን አካቶ ይወጣ የነበረው ፈተና ዘንድሮ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሰረት የ8ኛ ክፍል ትምህርቶችን ብቻ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናው በጥንቃቄ የሚሰጥ መሆኑን ተገንዝበው ኃላፊነት የማይሰማቸው አንዳንድ አካላት ለማህበራዊ ሚዲያዎች ለሚነዙት መሰረተቢስ ወሬ ጆሮ ሳይሰጡ ፈተናውን በአግባቡ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

የ8ኛ ክፍል ፈተናው ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት በአፍ መፍቻና  እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ከሰዓት በኋላ ደግሞ የስነ-ዜጋና የሒሳብ ትምህርትን በመስጠት የሚጀምር መሆኑን አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም