ቀጥታ፡

" ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪ የሚያደርግ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በመገንባት ላይ ነን '' -አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ) ፦ ከጊዜያዊ ውጤት ባለፈ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ተፎካካሪ የሚያደርግ የሴቶች እግር  ኳስ ቡድን በመገንባት ላይ ትኩረት አድርገናል ሲሉ የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን  አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ  ቡድን እ.አ.አ. በ2024 በፓሪስ ለሚያደርገው የኦሊምፒክ ስፖርት ጨዋታዎች  ዝግጅት እያደረገ ነው። 


 

በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ስፖርት ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዞን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከቻድ ጋር የተደለደለው ቡድን ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቡድኑ ላለበት ጨዋታ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ ሳምንት ማስቆጠራቸውን ገልፀዋል።

በእነዚህ ቀናት በጥሩ የቡድን መንፈስ በመጀመሪያው ዙር ከቻድ ጋር ላለባቸው ጨዋታ ዝግጅት እያደረጉ  መሆኑን ተናግረዋል።

በቡድኑ ጥቂት ልምድ ያላቸውና አዳዲስ ወጣቶችን በማካተት ልምምዳቸውን እያደረጉ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ለኦሊምፒክ ማጣሪያ ዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዶችን ለማድረግ ዕቅድ እንደነበራቸውና በዝናብ ምክንያት መቆራረጥ ቢኖረውም በሌሎች ዝግጅቶች ግን በተሳካ መልኩ ልምምዳቸውን እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

የቡድኑ ስብስብ ውስጥ ብዙ ተጨዋቾች ከ20 ዓመት በታች ለብሔራዊ ቡድኑ የተሻሉ የሚባሉ ልጆች እንደተመረጡም ነው የገለፁት።

ይህ ቡድን ከጊዜያዊ ውጤት በዘለለ በቀጣይ ሀገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ ውጤታማ የሆነ ቡድን ግንባታ ጭምር ትኩረት ተሰጥቶት እየሰራን ነው ብለዋል።

የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የተሻለ የሚባል ውጤት ያላቸው መሆናቸውን አስታውሰው፤ ክለቦችና ተቋማት ከዚህ በላይ ትኩረት አድርገው ከሰሩ ውጤታማ ቡድን ለመገንባት አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል ነው ያሉት።

በኦሊምፒክ የማጣሪያ ዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ  ቡድን አሁን ላይ 24 ተጨዋቾችን በስብስቡ ውስጥ እንዳሉም ነው አሰልጣኙ የተናገሩት።

የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ድልድል ኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር ከቻድ ጋር ከሐምሌ 3 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም.ባሉት ቀናት ታካሂዳለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም