ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአምስት ዓመታት የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ዕቅድ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን- የተመድ  የልማት ፕሮግራም 

አዲስ አበባ  ሰኔ 24 / 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም የተዘጋጀው ዕቅድ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ገለጸ።

መንግስት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በ20 ቢሊዮን ዶላር  የሚተገበር ብሔራዊ ዘላቂ የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ዕቅድ ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዳይሬክተር ቱርሃን ሳላህ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በድህረ ግጭት ወደ መልሶ ግንባታ ለመግባት የሚደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

የተመድ የልማት ፕሮግራም በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ለዕቅዱ ተግባራዊነት ለጋሽ ድርጅቶችን እና የልማት አጋሮችን የማስተባበር ስራን እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በሚቀጥለው አንድ ዓመት በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች በግጭት የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት በማቋቋም ሂደት የሚተገበር የድጋፍ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ዕቅዱን ለመንግስት ማቅረቡን ጠቁመው፤ ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በጦርነት የቆዩ ዜጎች ወደ መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመለሱ ለማድረግ በትምህርትና ግብርና ስራ ላይ በሚደረገው ጥረት ቀጣይነት ያለው እገዛ እናደርጋለን ብለዋል።

በድህረ ግጭት ማህበረሰቡን ወደ ዘላቂ ህይወት ለመመለስ የክልሎችና የፌደራል መንግስቱ ቅንጅት  ወሳኝነት ያለው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በሀገሪቱ ሰላምን ማጽናት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የልማት ፕሮግራሙም ለመልሶ ማቋቋሙ የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ ሰፊ ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ማቋቋም የሚያስችል ሀገራዊ ማዕቀፍ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል።

ባለፉት ዓመታት በተወሰኑ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በማህበራዊ፣ በምርት፣ በመሰረተ ልማት እና ባለብዙ ዘርፎች አጠቃላይ 22 ነጥብ 69 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውድመት መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር የጥናት ሪፖርት ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም