አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድባብ መናፈሻን ለመማር ማስተማር አገልግሎት ለማዋል የሚያስችለውን የመሬት ካርታ ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድባብ መናፈሻን ለመማር ማስተማር አገልግሎት ለማዋል የሚያስችለውን የመሬት ካርታ ተረከበ
አዲስ አበባ ሰኔ 24 / 2015 (ኢዜአ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድባብ መናፈሻን ለመማር ማስተማር አገልግሎት ለማዋል የሚያስችለውን የመሬት ካርታ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ተረከበ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ 8 ሺህ 470 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን የድባብ መናፈሻን የመሬት ካርታ ዛሬ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ኦሜጋ ተረክበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ የድባብ መናፈሻ ለዩኒቨርሲቲው ለተሰጠው ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል።
ዩኒቨርሲቲው ከተሰጠው ሀገራዊ ኃላፊነት አንጻር ለመማር ማስተማር ምቹ የሆኑ መሰረተ-ልማቶችን ማስፋፋት ላይ ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት አንስተው፤ ይህንንም ለማድረግ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ የግንባታ ማስፋፊያ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዛሬውም ዕለት ዩኒቨርሲቲው የድባብ መናፈሻን ለማልማት ከክፍለ ከተማው አመራር የመሬት ካርታ መቀበላቸውን በመናገር፤ ቦታው ለመማር ማስተማር የሚውል ምቹ የትምህርት ማዕከል እንዲሆን ለማድረግ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በቦታው ላይም ከ20 ፎቅ ያላነሰ የአይ ሲቲ ሴንተር እንደሚገነባ ገልፀው፤ ይህም የቦታውን መዝናኛነት ባገናዘበ መልኩ እንደሚሰራ ነው ያብራሩት።
ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ ዘመናት ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በትምህርት በማነጽ ለሁለንተናዊ የልማት እድገት የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ኦሜጋ፤ በዛሬው ዕለት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 8 ሺህ 470 ካሬ ሜትር ለመማር ማስተማሪያ አገልግሎት የሚውል የድባብ መናፈሻን የመሬት ካርታ አስረክበናል ብለዋል።
ባላፉት ሦስት ዓመታት ቦታው ለዩኒቨርሲቲው እንዲሰጥ ከተማ አስተዳደሩ የወሰነ ቢሆንም በሀገሪቱ ላይ ተፈጥረው የነበሩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳቢያ መፈጸም አልተቻለም ነው ያሉት።
በርክክቡ ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎችና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል።