የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርሙ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበረና ፖሊሳዊ የምርመራ ስነምግባርን የሚከተል ተቋም ገንብቷል-ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርምራ ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርሙ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበረና ፖሊሳዊ የምርመራ ስነምግባርን የሚከተል ተቋም ገንብቷል-ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ባካሔደው ሪፎርም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበረና ፖሊሳዊ የምርመራ ስነምግባርን የሚከተል ተቋም መገንባቱን የጠቅላይ መምሪያው ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በ2015 በጀት ዓመት ለተመዘገቡ ስኬቶች የላቀ አስተዋፅአ ለነበራቸው አመራሮች፣ አባላትና ባለድርሻ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሐግብር በሚሊኒየም አዳራሽ እያካሄደ ነው።
በመርሐግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል እና የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ደመላሽ ገብረሚካኤል፣የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የለውጥ ስራዎች ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉም ተገልጿል።
ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በዚሁ ወቅት፤ ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ በህዝብና ሀገር ላይ የተፈጸሙ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመርመር አጥፊዎችን ለህግ ሲያቀርብ ቆይቷል ብለዋል።
ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆንም በተለያዩ አካባቢዎች የታቀዱ ትልልቅ ወንጀሎችን ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመቆጣጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
በዚሁ ወቅት ሲያካሒድ የቆየው የወንጀል ምርምራ ተግባር የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ያከበሩና የፖሊስ የምርመራ ሰነ-ምግባር መርህን የተከተሉ እንዲሆኑ ለማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሚካሔዱ የምርመራ ስራዎች በተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊት ላይ ብቻ ያተኮሩ፤ ህግን መሰረት ያደረጉ ናቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ይሕም የተቋሙን የለውጥ ስራ ውጤታማነት ያመላክታል ብለዋል።
ሙያዊ ብቃትን ያረጋገጠ አካታች እና በህዝብ ታማኝ የሆነ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የመገንባት ራዕይ በመሰነቅም ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ መምሪያው ባከናወነው የሪፎርም ስራ ዓለም አቀፍ የፖሊስ የምርመራ ደረጃን በማሟላት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዙ የምርመራ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዘመናዊ የቃል መቀበያ ቢሮዎች፣ ተጠርጣሪዎች ከህግ አማካሪዎቻቸው ጋር በነጻነት የሚመካከሩበት ስፍራ፣ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ማረፊያ እና መጠየቂያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
የተጠርጣሪ ምዝገባና አስተዳደር መረጃዎች ሙሉ በሙሉ በኮምፒውተር የተደራጁ መሆኑንም አንስተዋል።