ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴ ስኬታማነት ድርሻችንን እንወጣለን - የካፋ ዞን ተወካዮች

ቦንጋ ሰኔ 24 / 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንቅስቃሴ ስኬታማ በማድረግ ድርሻቸውን እንደሚወጡ በደቡብ  ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዘቦች ክልል የካፋ ዞን የህብረተሰብ ተወካዮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቦንጋ ከተማ ያካሄደው የክልል ተወካዮችን የተመረጡበት መድረክ ተጠናቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የካፋ ዞን ተወካዮች ኮሚሽኑ የጀመረው ስራ ስኬታማ ለማድረግ ድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል። 

ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ችግር አውጥቶ ጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር የውስጥ ችግሮቻችንን በመነጋገርና በሰላማዊ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት የኮሚሽኑ መቋቋም ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ታመነ ንጋቱ ናቸው።

ይህም የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ቀድሞ የምንታወቅበት በአብሮነትና በመቻቻል ለመኖር ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል ።

በመሆኑም ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የማህረሰቡ ክፍሎችን በማንቃት ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አቶ ታመነ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ለማሳተፍ የሚያደርገው ጥረት አካታችነቱና አሳታፊነቱን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባለፈ፤ ሁሉም ሀገራዊ ስሜት እንዲኖረው ያደርጋል ሲሉም አክለዋል።


 

ወጣት ሰናይት ወልደሰንበት ደግሞ ኮሚሽኑ ለግጭትና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ከታች ጀምሮ በመለየትና ምክክር በማድረግ በሚመለከታቸው አካላት እንዲፈቱ ያደርጋል ብላለች።

''ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን እኔም የበኩሌን እወጣለሁ'' ስትልም አስተያቷን ሰጥታለች። 

"የኔ ብቻ ይበልጣል፤ እኔ አውቅልሀለሁ የሚል አስተሳሰብ ሰፍቶ በሀገራችን ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው" ያሉት የጨና ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሱሌይማን አባፊጣ፣ ''ከዚህ አስተሳሰብ ወጥተን ለሀገር ልማትና ሰላም በጋራ ልንሰራ ይገባል'' ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያን ለመገንባትና ሰላሟን ለማስጠበቅ መነጋገርና ችግሮችን በተረጋጋ መንገድ መፍታት እንደሚያስፈልግ አመልክተው፣ ለዚህ ደግሞ ወሳኝ የሆነው ምክክር ሂደት ስኬታማነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም