ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም ፈጥሯል - የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ 

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘትና ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ገለጹ፡፡

የባህር ዳር ከተማ ምቹ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ተከትሎ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ እየወሰዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሁሉም አካባቢዎች ተቀዛቅዞ የነበረውን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አነቃቅቶታል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከውጭ የሚያስገቡትን ምርት የሚያስቀር ከዚያም አልፎ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚያስችሉ ትላልቅ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡


 

በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘይት ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሦስተኛ ደረጃ የያዘው የዘይት ፋብሪካ በባህር ዳር ከተማ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ሌሎችም ትላልቅ የመኖ፣ ግራናይት፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ከፍተኛ ዘይት የማምረት አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች በቅርቡ ተመርቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር እንደ መንገድ፣ መብራትና ውሃ  ያሉ የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎችን እያሟላ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታማነታቸውን ለማሳደግ የሚያቀርቡት የማስፋፊያ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የሙሌ እንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የቅመማ ባለሙያ ዶክተር አዳነ አማረ፤ 99 በመቶ የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም 18 ዓይነት የእንስሳት መኖ እንደሚያመርቱ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በዓይነቱ የተለየ የዶሮና የግመል መኖ በማምረት የግብይት አድማሳቸውን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የገደፋው አውቶሞቲቭ ማኑፋክቸሪንግ ባለቤት አቶ ገደፋው ይስማው፤ ከውጭ የሚገቡ ተሳቢ ተሽከርካሪዎችና የነዳጅ ታንከሮችን በመገጣጠም ቴክኖሎጂውን እያስፋፉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የአለባቸውና ማስተዋል ሽርክና ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ይርጋ አለባቸው፤ ከ6 ሺህ ብር ካፒታል የትልቅ ፋብሪካ ባለቤት ለመሆን መብቃታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዜጎች የሀገር ውስጥ ምርትን እንዲጠቀሙ ግንዛቤ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘንድ መነቃቃት ፈጥሯል የሚሉት አምራቾቹ፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት ከውጭ ምንዛሬና ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ ድጋፍ ቢያደርግልን ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እና በስፋት ለውጭ ገበያ ማምረት እንችላለን ብለዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም