በሀገሪቱ በወንጀል ጉዳዮች ፍትህ ለመስጠት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ትኩረት ተሰጥቷል--ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ በወንጀል ጉዳዮች ፍትህ ለመስጠት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ትኩረት ተሰጥቷል--ኮሚሽኑ
ሀዋሳ ሰኔ 24/2015 (ኢዜአ) በሀገሪቱ በወንጀል ጉዳዮች ፍትህ ለመስጠት በሚደረግ ሂደት ውስጥ የዜጎችን ሰብኣዊ መብቶች ለማስከበር ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በደቡብ፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ 75 ፖሊስ ጣቢዎች ላይ ባደረገው ክትትል ግኝቶችና ምክረ ሀሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ ከተማ መክሯል።
በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ምርመራና ክትትል ክፍል ሃላፊ ዶክተር ሚዛኔ አባተ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በህገ መንግስቱና በሌሎች ሰነዶች የተቀመጡ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችና ድንጋጌዎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው።
በዋናነትም በወንጀል ፍትህ ሂደት ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረግ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ለሂደቱ ተፈጻሚነት ፖሊስን ጨምሮ የፍትህ ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በተቋማቱ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም የመከታተልና ችግሮች ሲከሰቱም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንዲፈቱ የማድረግ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ሃላፊው አስረድተዋል።
በ2015 በጀት ዓመት 11 ወራት ከ384 በሚበልጡ የተጠርጣሪ ማቆያ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ማድረጋቸውንና ከ1 ሺህ 986 በላይ አቤቱታዎች መቀበላቸውንም ገልጸዋል።
በተጠርጣሪ ማቆያ ጣቢያዎች የተሻሻሉ ተግባራት ቢኖሩም ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ በዋስትና የተለቀቁ ሰዎችን የማሰፈጸም ችግሮች መሰተዋላቸውን ጠቅሰዋል።
በችግሮቹ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረኮች እንደሚካሄዱና የዛሬው መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን አመልክተው፣ አብዛኞቹ ምክረ ሃሳቦች በባለድርሻ ድርሻ አካላት እንደሚተገበሩም ተናግረዋል።
የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች እንዲፈጸሙ ለማድረግ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ይሰራል ብለዋል።
በኮሚሽኑ የሀዋሳ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በሲዳማ፣ በደቡብና በደቡብ ምእራብ ኢትየጵያ ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ 75 ፖሊስ ጣቢያዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ክትትል መደረጉን ገልጸዋል።
በምርመራ ሂደት ውስጥ ይታይ የነበረው የሃይል አጠቃቀም መቅረቱን ገልጸው፤ የተጠርጣሪዎች የመዝገብ አያያዝና መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚደረገውን ጥረትንም በጥንካሬ አንስተዋል።
የተጠርጣሪ ማቆያ ክፍሎች ጥበት፣ የንጽህና ጉድለትና ተጠሪጣሪን በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ያለማቅረብ ችግሮች በአብዛኞቹ ፖሊስ ጣቢያዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በታዩ ክፍተቶች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ወደ መፍትሄ መድረስ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፣ አንዳንዶቹ ጉዳዮች በፍጥነት ምላሽ ያገኙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ጆሃር ኤሊሶ እንደገለጹት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ በጥናት የለያቸው ግኝቶች በተጠርጣሪ ማቆያዎች ውስጥ በተጨባጭ እንደሚታዩ ገልጸዋል።
በዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የታዩ ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰሩ ጠቅሰው፣ በተለይ ተጠሪጣሪዎችን በ48 ሰዓት ፍርድ ያለማቅረብ ችግር ላይ የግንዛቤ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የምርመራ ዘርፍ ኮሚሽነር ሃይሶ አለሙ በበኩላቸው በኮሚሽኑ የተለዩ ግኝቶች በርካቶቹ የሚታወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ለዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከሚሽኑ ክትትል ያደረገባቸው 75 ፖሊስ ጣቢያዎች 28ቱ ከሲዳማ፣ 41ዱ ከደቡብ፣ ስድስቱ ደግሞ ከደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ ሲሆኑ፣ በመድረኩ ከሲዳማና ከደቡብ ክልሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።