ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊ አብሮነትን፣ የጋራ እሴትና ጥብቅ ትስስርን በማጎልበት ለብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ አንድነት  በትብብር መስራት አለብን- ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን፣ የጋራ እሴትና ጥብቅ ትስስርን በማጎልበት ለብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ አንድነት በትብብር መስራት አለብን ሲሉ የሰላም ሚኒስትርሩ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የጋራ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብዝኃ-ማንነትን መገንባት እንደሚገባም ምሁራን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "አገራዊ እሴቶች ለብሔራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም፤ ኢትዮጵያ የዜጎች የአብሮነት ሕብረ-ቀለም የሆኑ የተለያዩ ሃይማኖቶች ቋንቋና አስተሳሰቦች ሀገር ብትሆንም ከሀገራዊ ማንነት ይልቅ የግለሰብና የቡድን ማንነት ገዥ ኃይል ሆኖ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለግልና ለቡድን ጥቅም የተሰጠው ምልከታና ትኩረት በሀገራዊ ጥቅም፣ የጋራ ማንነትና ብሔራዊ መግባባት ላይ መዘናጋት የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊ አብሮነትን፣ የጋራ እሴትና ጥብቅ ትስስርን በማጎልበት ለብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ አንድነት በትብብር መስራት አለብን ብለዋል።

በሉላዊነት የተሳሰረው ዓለም ለብዙ ነገር የቀረበ በመሆኑ ለብሄራዊ ጥቅምና ሉአላዊነት መከበር አብሮነትን ማጠንከር ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን በጋራ መመከት ይገባናል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ፤ "ብሔራዊ ጥቅም ለአገር ግንባታ" በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ባቀረቡት ጽሑፍ፤ ብሔራዊ ጥቅም ባልተከበረበት ሀገር የሚከበር የንዑስ ጥቅም የለም ብለዋል፡፡


 

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ተመራማሪ ዶክተር ሮባ ጴጥሮስ፤ "ብሔራዊ እሴቶቻችንና አብሮነት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ "በኢትዮጵያ በባህል፣ በኢኮኖሚና በመሰል ጉዳዮች ላይ የተፈጠረው መራራቅ በማኅበረሰቡ ወይስ ማኅበረሰቡን በሚዘውረው ቡድን" የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ትናንትም የነበረ ዛሬም ያለ በባህል፣ በሃይማኖት እና በሌሎች ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮች የተሳሰረ ሕብረተሰብ እንዳለ ጠቅሰው፤ መሠረታዊ ልዩነቱ "እኔ አውቅልሀለው" በሚለው ኃይል ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በተሳሳተና ልዩነት የሚፈጥሩ ትርክቶችን  ብዝኃነትን በሚሰብኩ የሕግ ማዕቀፎች መቀየር ይገባል ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ የሆነችው ናይጄሪያ በሕገ-መንግሥቷ ላይ ቅድሚያ የምትሰጠው ብዝኃነትን ያከበረ አንድነት መሆኑን በመጥቀስ፡፡


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፤ "ብሔራዊ ማንነት ለዘላቂ ሀገራዊ አንድነት" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሀሳብ፤ ኢትዮጵያ የብዝኃነት ማበልጸጊያ ማዕከል ሊኖራት ይገባል ብለዋል፡፡

ቤተሰብ ልጆቹን የግብረገብነት ትምህርት የማስተማር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትር  ብናልፍ አንዷለም፤ በኢትዮጵያ ለመገንባት የታሰበው ማንነት በመደመር እሳቤ ሕብረ- ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሊዓላዊነትና ብሔራዊ አንድነት ላይ የምንነጋገረው ሀገር ስላለን መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መነጋገርና መግባባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።   

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም