ቀጥታ፡

ተቋማቱ  ስብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል-የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

ሰመራ ሰኔ 23 /2015 (ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት ስብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት የስራ እንቅስቃሴና ዓመታዊ ዕቅድ አፈፃፀምን ዛሬ ገምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴው ግምገማውን ያካሄደው በዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ በዋናነት በሚሰሩ  የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፣ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲሁም ከመገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን  አፋር ቅርንጫፎች ላይ ነው። 

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ ከድር ኢድሪስ በክልሉ የሚገኙ የፌዴራል ተቋማት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ በትኩረት  መሠራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

አቶ ከድር አክለውም ተቋማቱ ከተሰጣቸው ተግባራት አኳያ  ተልዕኮና ኀላፊነታቸውን በበለጠ በመወጣት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ተቋማቱ ያለባቸውን የበጀትና የሰው ሀይል እጥረቶች ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ጋሻው ዳኘው በበኩላቸው   ህብረተሰቡ  በዴምክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የጎላ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ለተግባራዊነቱም ተቋማቱ ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አፋር ቅርንጫፍ ተጠሪ  አቶ ኡስማን አህመድ በበጀት ዓመቱ ኮሚሽኑ በተሠጠው ስልጣን መሠረት በራስ ተነሣሽነትና  በሌሎች ጥቆማ መሠረት 65 አቤቱታዎችን ተቀብሎ፣ ከ10ሩ  በስተቀር አግባብ ባለው መሠረት መሥተናገዳቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም