ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል ደረጃ ለሚካሄደው የአጀንዳ ልየታ መድረክ የሚሳተፉ 820 ተወካዮች ተለይተዋል---ኮሚሽኑ

ሀዋሳ ሰኔ 23/2015 (ኢዜአ) :-ለአገራዊ ምክክሩ በሲዳማ ክልል ደረጃ ለሚካሄደው የአጀንዳ ልየታ መድረክ የሚሳተፉ 820 ተወካዮች መለየታቸውን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል በሀገራዊ ምክክር መድረኩ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫን በማስመልከት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንደገለጹት፣ በሲዳማ ክልል ከ37 ወረዳዎች፣ ከሁሉም ክፍለ ከተሞችና ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊዎችን ለመለየት የሚያስችሉ መድረኮች ተካሂደዋል።

በዚህም ከ22 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙባቸው 20 መድረኮች መካሄዳቸውን ነው የገለጹት።

በመድረኩ ከሴቶች፣ ከወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እንዲሁም እድሮችና የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ ከዘጠኝ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከእያንዳንዱ ወረዳ በየማህበረሰቡ ሁለት ተወካዮች ከአንድ ተጠባባቂ ጋር በተሳታፊዎች ተመርጠው ለምክክሩ እንዲወከሉ መደረጉን ጠቁመዋል።

በዚህ ሂደትም በክልል ደረጃ በሚካሄደው የአጀንዳ ልየታ መድረክ የሚሳተፉ 820 ተወካዮች መለየታቸውን ዶክተር ዮናስ አስታውቀዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በውክልና ሂደቱ የየማህበረሰቡ ተወካዮች የተመረጡበት መንገድ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልጽና ከፍተኛ ተሳትፎ የታየበት ነው። 


 

ሌላው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ በክልሉ ያካሄዳቸው መድረኮች ከተሳታፊ ብዛትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማካተት አንጻርም ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል። 

ለሂደቱ መሳካት የክልሉ ህዝብ ያበረከተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

"በቀጣይ በተመሳሳይ መልኩ በክልል ደረጃ የሚሳተፉ ተወካዮችን ከየተቋማቱ የመለየት ሥራ ይከናወናል" ሲሉም ዶክተር አምባዬ አመለክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች ከተወከሉ ተወካዮች ጋር በጋራ የአጀንዳ ልየታ መድረክ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ላከናወነው ስኬታማ ሥራ የክልሉ ህዝብ፣ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበር ጠቁመው፣  ለዚህም በኮሚሽኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም