በ2015 በጀት ዓመት በበጎ ፈቃደኞች 53 ሺህ ዩኒት ደም ተለግሷል - የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በ2015 በጀት ዓመት በበጎ ፈቃደኞች 53 ሺህ ዩኒት ደም ተለግሷል - የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ)፡-በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር 53 ሺህ ዩኒት ደም መለገሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ይህን ያለው የኢትዮጵያ ደምና ህብረ- ህዋስ ባንክ ለበጎ ፈቃደኞች የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ባካሔደበት ወቅት ነው፡፡
በኮሚሽኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር ዳዊት ሙሉጌታ እንዳሉት፣ 53 ሺህ ዩኒት ደሙ የተለገሰው የተለያዩ ሁነቶችን ተጠቅሞ በተደረገ የማስተባበር ስራ ነው፡፡
በጎ ፈቃደኞች አንድ ጊዜ ደም በመለገሳቸው የሰዎችን ሂወት ማዳን እንደሚችሉ በማመን ደም ለግሰዋል ብለዋል።
የደም ልገሳው የተካሄደው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮና ከኢትዮጵያ ደምና ህብር- ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጋር በመቀናጀት ነው ብለዋል፡፡
አቶ ዳዊት ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በቀጣዮቹ ወራት ''በጎ ፈቃደኝነት ለዘላቂ አብሮነት'' በሚል መሪ ሃሳብ የበጎ ፈቃደኝነት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በመዲናዋ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር 35 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብእየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህን እቅድ እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በትብብር ከተሰራ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያለፈው ስራ ምስክር ነው ብለዋል፡፡
በጎ ፈቃደኝነት የመረዳዳት ስሜትን የሚያጎለብት አብሮነትን የሚያጠናክር ተግባር በመሆኑ ሁሉም ሰው የዚህ ሰናይ ተግባር ተቋዳሽ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማዕድ ማጋራት፣ የቤት እድሳትና ሌሎች መሰል ተግባራት የኮሚሽኑ የወቅቱ የትኩረት ማዕከል መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡